ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ሽግግር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሚና ጉልህ እንደሆነ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ተባለ፡፡

“ለኢንዱስትሪ እድገታችን ቴክኒክና ሙያ የመጀመሪያ ምርጫችን” በሚል መሪ ቃል 9ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ንቅናቄ ሳምንት ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 1 በኤግዚቢሽን ማእከል እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው 9ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የንቅናቄ ሳምንት ሀገሪቱ እየተከተለች ያለውን ኢንዱስትሪ መር ስትራቴጂ ለማፋጠንና በተለይ የሀገር ውስጥ አዳድስ ፈጠራዎችን በማቅረብ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ ቴክኒክና ሙያ ያለውን ግንዛቤ እንዲዳብር ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው የንቅናቄ ሳምንቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዚህ 9ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የንቅናቄ ሳምንት ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ከ100 በላይ የፈጠራ ውጤቶች በኤግዚብሽን ማእከል ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ሲሆን የንግድ ትስስር የሚፈጥርበትን አማራጮችም ለማስፋት እድል ይከፍታል ተብሏል።