ከ296 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ አነስተኛ የፀሀይ ኃይል ማመንጫዎች ሊገነቡ ነው ተባለ

ከ296 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 12 አነስተኛ የፀሀይ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የፀሀይ ሀይል ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ ደቡብና አማራ ክልሎች የሚገነቡ ሲሆን፤ ግንባታው የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የብሄራዊ ኤሌክትሪክ ሀይል መረብ በማይደርስባቸው ናቸው፡፡

በተጨማሪም በሶማሌ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች አንዳንድ የፀሀይ ሀይል ፕሮጀክቶችእንደሚገነቡ ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ 67 ሺህ 700 ቤቶች የአሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ያስችላሉም ተብሏል፡፡

መንግስት ከፀሀይ፣ ንፋስ እና ሌሎች ታዳሽ ሀይሎች 35 ሚሊየን ህዝብ የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኝ እየሰራ ሲሆን፤ በዚህም በሀሪቱ በሚገኙ 250 ከተሞች 6 ሚሊየን የሚሆኑ ቤቶች ከታዳሽ ሀይሎች የኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይ 25 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የዲዛይን ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ ለግንባታው 15 ሚሊየን ዶላር በብድርና ልገሳ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እንደተገኘ ተነግሯል፡፡

በሀገሪቱ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለማሰራት ከአለም ባንክ 400 ሚሊየን ዶላር እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ 100 ሚሊየን ዶላር በብድርና ድጋፍ ተገኝቷልም ተብሏል፡፡

ግንባታውን ለማከናወን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቻይና እና የስፔን አለም አቀፍ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡