በቨርጂኒያ በደረሰ ጥቃት 12 ሰዎች ተገደሉ

በአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት በአንድ የመንግስት መሥሪያ ቤት ውስጥ በተከፈተ የተኩስ እሩምታ 12 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ተገለጸ፡፡

ጉዳን አስመልክቶ ፖሊስ እንደገለጸው ተጠርጣሪው በከተማዋ የባህር ዳርቻ ለረዥም ጊዜ ያገለገለና አሁንም እየሠራ ያለ የመንግሥት ተቀጣሪ ሲሆን፤ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ባሉ ባልደረቦቹ ላይ በመተኮስ ጉዳት አድርሷል።

የተጠርጣሪው ማንነት እስከአሁን ይፋ ባይደረግም ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ እንደተገደለ ተገልጿል።

የአካባቢው ባለስልጣናት አንድ የፖሊስ ባልደረባ መጎዳቱንም ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው የቨርጂኒያ የባህር ዳርቻ ከተማ አስተዳደር ሕንፃዎች በሚገኙበት ስፍራ ሲሆን፤ ጥቃት መድረሱ አንደተሰማ ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ ወደስፍራው የሚገቡና የሚወጡትን በማገድ ሠራተኞቹን ከህንፃው አስወጥቷል ነው የተባለው።

እንደ የፖሊስ ኃላፊው ጀምስ ሴሬቫ ገለጻ ከሟቾቹ መካከል አንዱ ከመኪናው ውጪ የተገደለ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ግን በህንፃው ውስጥ ሳሉ ተገድለዋል። አራት የፖሊስ ባልደረቦች ወደ ህንፃው በመግባት ጥቃት አድራሹን በማግኘት ወዲያው የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ መገደሉንም ገልፀዋል።

የ12ቱ ሟቾችና የተጠርጣሪው ማንነት እስካሁን ድረስ ይፋ እንዳልተደረገና የሟቾቹ ማንነት ለቤተሰባቸው ከተነገረ በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ፖሊስን ጨምሮ አራት ሰዎች መጎዳታቸው የታወቀ ሲሆን፣ የጉዳታቸው መጠን ግን አልተገለፀም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)