የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ የ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ እየተወያየ ነው።
በምክር ቤቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 386 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ሆኖ በተዘጋጀው ረቂቅ በጀት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
የተዘጋጀው የረቂቅ በጀት እቅድ ከ2011 በጀት አመት አንጻር የ6 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወይንም የ1 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሬ አለው ።
ከተዘጋጀው ጠቅላላ ረቂቅ በጀት ውስጥ፥ ለመደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል 130 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እና ለክልል መንግስታት ድጋፍ 140 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚውል ይሆናል።
የካፒታል በጀት ወጪ አሸፋፈኑ ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ 94 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ቀሪው ከውጭ ሀገር የሚገኝ ብድርና እርዳታ ሌሎች ገቢዎች የሚገኝ ሲሆን፥ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ግብርና እና የከተማ ልማት ወጪዎች ይሆናል።
ከመደበኛ ወጪው 109 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ውስጥ 34 በመቶው የደሞዝ አበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች፣ ቀሪው 66 በመቶ ለብድር ክፍያ፣ ለልዩ ልዩ ወጪዎችና ለሌሎች ክፍያዎች የሚውል ነው።
386 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመንግስት 2012 በጀት አመት ወጪ ሲታቀድ የመንግስት ገቢ ደግሞ በተመሳሳይ 289 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ይሆናል ተብሎ ነው የታሰበው።