የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ የ2012 በጀት 70 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር እንዲሆን ወሰነ

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ የ2012 በጀት 70 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር እንዲሆን ወሰነ፡፡

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት (ካቢኔ) ሰኔ 30/2011 ባካሄደዉ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ዉሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

ካቢኔዉ ለ2012 የክልሉ አመታዊ በጀት 70.16 ቢሊየን ብር እንዲሆን በቀረበዉ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ዉይይት ካካሄደ በኋላ ለጨፌ ኦሮሚያ ቀርቦ እንዲፀድቅ የዉሳኔ ሀሳብ አሳልፏል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ካቢኔ በ2011 የበጀት አመት የክልሉ የአስፈፃሚ አካላት ዋና ዋና ጉዳዮች እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን የገመገመ ሲሆን፣ የ2012 የክልሉ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም በመወያየት ዉሳኔ አስተላልፏል፡፡

በ2011 የክልሉን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎቶችን ለማሟላት በፀጥታና ልማቱ ዘርፍ ዉጤታማ ተግባራት መከናወናቸዉን ገምግሟል፡፡

የክልሉን ሰላም በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የህዝቦች ወንድማማችነትና የጋራ እሴቶች እንዲጎለብቱ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸዉን ነዉ ካቢኔዉ የገመገመዉ፡፡

በመንግስትና በህዝቡ መካከል ተቀራርቦ የመስራትና የህዝቡ ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ የበለጠ በመጠናከሩ የተጀመረዉ አገራዊና ክልላዊ ለዉጡ በስኬት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

በ2012 የበጀት አመትም አገራዊ ለዉጡ በዉጤት ታጅቦ እንዲጓዝ የክልሉን ህግና የአገሪቷን ህጎች መሰረት ያደረገ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና የህዝቡን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ ማስፈን በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም በካቢነዉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ ገበያ ተኮር ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲመረቱ በአቅርቦት፣ በክትትልና ድጋፍ የተሻለ አፈፃፀም እንዲከናወን ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ለ1.1 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠር ሰፊ ስራ ይሰራል ነው የተባለው፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቶችን ማፋጠን፣ ነባር የመንገድና የዉሃ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራትና በሁለንተናዊ አገልግሎት የህዝቡን ፍላጎት ሊያረካ የሚችል ጥራት ያለዉ ስራ እንዲሚሰራ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የስራ ባህል ማሻሻል፣ ሌት ተቀን መስራት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የህዝቡን ቱባ ባህሎችን መቀመር፣ አንድነትና ዉይይቶችን ማጠናከርም ዋነኞቹ የእቅዱ አፈፃፀም ስልቶች ናቸዉ፡፡

ካቢኔዉ በዚህ ስበሰባዉ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለዉ በቅርቡ ወደ ቀዬያቸዉ ለተመለሱ ዜጎች የእርሻ መሳሪያ ግዢ የሚዉል የ 43.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍም አፅድቋል፡፡

ድጋፉ ለተፈናቃይ ወገኖች ከተሰበሰበዉ ብር ወጪ የሚደረግ ነዉ፡፡

በመጨረሻም የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ የኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎትን ለመወሰን የቀረበዉን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለጨፌ ኦሮሚያ መምራቱን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን በላከልን መግለጫ አስታውቋል፡፡