ፕሬዚዳንቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ለልማትና ዲሞክራሲ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 28/2008(ዋኢማ)-ዘመናዊ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የልማትና የዲሞክራሲ ድሎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ዛሬ በሂልተን ሆቴል አገር ዓቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ማብሰሪያ መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፤ አገሪቱ የምትከተለውን ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ ኩነቶች በዘመናዊ መልኩ ሊመዘገቡ ይገባል፡፡

አገራዊ ዕቅዶችን ዕውን ለማድረግና የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ቀጣይነት ያለው፣ወጥና ሁሉን ዓቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓት እንዲዘረጋ መንግስት ራሱን የቻለ ኤጄንሲ እንዲቋቋም ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ህገ መንግስቱ ዕውቅና የሰጣቸውን የዜጎችን መብትና ነፃነት በማክበርና በማስከበር፤ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትን በሁሉም የአስተዳደር እርከን ለማስፈንም ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ ያስገነዘቡት፡፡

አክለውም የሚወጡት ህጎች፣ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ እንዲፈፀሙም ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዋና ዐቃቤ ህግና የወሳኝ ኩነት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው አምባዬ በበኩላቸው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ቀደም ሲል በዘልማድ ሲከናወን የነበረውን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓትን ለማዘመን እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ወሳኝ ኩነቶች ሲከሰቱ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለመመዝገብ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የፌዴራል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጄንሲን በማቋቋም በሰው ኃይልና በግብዓቶች እንዲያሟላ ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በፌዴራል መንግስት 101 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጄንሲንዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤልሳ ተስፋይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ኤጄንሲው የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት  ለመወጣት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎችን የማሰልጠንና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራትን በስፋት ማከናወኑን ነው ያብራሩት፡፡

በሚዛናዊ ክፍያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች የሚሸፈን 247 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል፡፡

ወሳኝ ኩነቶችን በማስመዝገብ ግዴታ በመሆኑ የጤና ተቋማት፣የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም በንቃት በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡