የናሚቢያዋ ቀዳማዊ እመቤት ፔኔሁፒፎ ፓሃምባ ስልጣናቸውን ከቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን ተረከቡ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2004 (ዋኢማ) – ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ድርጅት ስልጣናቸውን የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ለተመረጡት የናሚቢያ ቀዳማዊ እመቤት ፔኔሁፒፎ ፖሃምባ ትናንት አስረከቡ።

የሥልጣን ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ትናንት በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል በተካሄደበት ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ኤዘብ ለናሚቢያዋ አቻቸው የእንኳን ደስ አሎትና መጪው የስራ ዘመን የስኬት እንዲሆንላቸው ተመኝተውላቸዋል።

በአፍሪካ የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የእናቶችን ሞቶ ለመቀነስ የሴቶችን አመራር ሰጪነት ሚና ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን በሥልጣን ርክክቡ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ አሳስበዋል።

ሴቶች ከኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ እራሳቸውን እንዲጠብቁ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህም ከእናት ወደ ፅንህ የኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ እንዳይተላለፍ ለማድረግ  ይረዳል ብለዋል።

ወይዘሮ አዜብ መስፍን ድርጅቱን ላለፉት ሶስት አመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ባገለገሉባቸው ወቅት በአዲስ አበባ ቋሚ ሴክሬተሪያት በማቋቋም፣ ጠንካራ የግንኙነት እስትራቴጂ በመመስረት፣ ለአስተዳደርና ፋይናንስ አሰራር ሊያገለግል የሚችል መመሪያ፣ እቅድና ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችም ገቢ በማሰባሰብ በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ቀዳማዊ እመቤት አዜብ ለድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርጉ ለነበሩት ለዩኤንኤድስ፣ ዩኤኤፍፒና ለፈረንሳይ መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ከአዲሷ ፕሬዚዳንት ጋርም ተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የናሚቢያ ቀዳማዊ እመቤት ፔኔሁፒፎ ፖሃምባ በበኩላቸው፤ በቆይታቸው ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን ድርጅቱን ካደረሱበት ደረጃ በመረከብ በተጠናከረ ሁኔታ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ፣ እቅድና ፕሮግራም በጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

እንደ ናሚቢያዋ ቀዳማዊ እመቤት ፔኔሁፒፎ ፖሃምባ ገለፃ በመጪዎቹ አመታት የድርጅቱን ተደራሽነት በማስፋፋት፣ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል፣ እንክብካቤና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ  ላይ በማተኮር እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ የድርጅቱን አባላት በማስፋት ላይም ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚችል ተናግረዋል።

አዲሷ የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ድርጅት ፕሬዚዳንት ፖሃመባ ባለፈው ዓመት ሰኔ መጨረሻ በጊኔ ማላቡ በተካሄደው አስረኛው አጠቃላይ የድርጅቱ ስብሰባ ላይ የተመረጡ ሲሆን፤ ቀዳማዊት ክብርት ወይዘሮ አዜብ መስፍንም የስትሪንግ ኮሚቴ አባል አድርጎ መምረጡ የሚታወስ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።