ከ80 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ ታክስ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንደሚሰበሰብ ተገለፀ

አዲስ አበባ መስከረም 27/2004 (ዋኢማ) – ከ80 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ ታክስ የሚሰበሰበው ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች በመሆኑ የተለየ ትኩረትና የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

በሀገሪቱ ከፍተኛው የሀገር ውስጥ ታክስ የሚሰበሰበው ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሲሆን፤ ግብር ከፋዮች ከባለስልጣኑ ጋር ተቀራርበውና ተደጋግፈው በመስራት የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግና በአሰራር ላይ የሚፈጠሩ ስህተቶችን በማሻሻል በተያዘው የበጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ እቅድ ማሳካት እንደሚገባም ተገልጿል።

ባለስልጣኑ የሚከሰቱ ችግሮችንም በወቅቱ ለማስተካከል ዝግጁ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ለስኬቱም ሁሉም አካላት በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተገልጿል።

ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ የሰበሰቢ ሲሆን፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መግለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።