የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች የሚያስተዋወቅ ዝግጅት ለንደን በሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2004/ዋኢማ/ – የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎችን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ዝግጅት ለንደን በሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ተካሄደ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎችና መስህቦችን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ዝግጅት በለንደን ተካሂዷል፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ በዚሁ ወቅት ባሳሙት ንግግር አገሪቱ ጎብኚዎችን መሳብ የሚችሉ በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች እንዳሏት ገልጸዋል፡፡

አጋጣሚው ኢትዮጵያ ያሏትን ሰፊ የቱሪስት መስህቦች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ መልካም ዕድል የፈጠረ ነው ማለታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊና አማካሪ እንዲሁም የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ወርቅነህ አክሊሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪስት መስህቦችን ለዓለም በማስተዋወቅ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የማስፋፋትና የአገሪቷን መስህቦች የማስተዋወቅ ሥራ የሁሉም ወገኖች የጋራ ጥረት መኖር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዝግጀቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የትራቭል ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያን የሚያስቃኝ”ትራቭልስ ስሩ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በታዋቂው የጎዞ ማስታወሻ ጸሃፊ ፍራንሴስ ሊንዚ ጎርደን ሰፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በዝግጅቱ በዓለም የጉዞ ገበያ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን ጨምሮ ከ150 በላይ የቱር ኦፕሬተሮችና ጸሃፍት ተካፋይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።