አዲስ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅት እየተካሄደ ነው – የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2004 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ በ2005 በጀት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለጹ።

በተለያዩ እርከኖች ላይ በሚገኙ መንግስታት መካከል ስለሚደረግ የፊስካል/ ፋይናንስ ሽግግር ሥርዓት ላይ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የተዘጋጀ የሁለት ቀናት ስልጠና ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ተጀመረ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ካሳ ተክለብርሃን ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ምክር ቤቱ ከ2005 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን በሁሉም ክልሎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አዲስ የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።

የሚዘጋጀው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ካለፉት ጊዜያት ቀመሮች በተሻለ መልኩ ፍትሃዊ እንዲሆን ግልጽነት፣ ተጨባጭነት ያለውና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እንዲዘጋጅ ይረደጋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር የሚሰራው እስከ 2004 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ የሚያገለግል መሆኑንም ገልጸዋል።

የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ የሚቀመጥ ሳይሆን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ በመሆኑ አዲስ የሚዘጋጀው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ የሚዘጋጅ መሆኑን አፈ ጉባዔ ካሳ ገልጸዋል።

በየደረጃው ያለው የኀብረተሰብ ክፍል በቀመር ዝግጅት፣ በወቅታዊ የቀመር ኢኮኖሚ ክፍፍልና በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች የተገኙት ውጤቶች በሕገ-መንግስቱ መረጋገጥ መሆኑን የሚያሳውቅ ሥራዎች እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

መንግስት አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የነደፈውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሎች ከምንጊዜውም በላይ ያላቸውን የልማት አቅም አሟጠው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቀዋል።

አዲስ የሚዘጋጀው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ከማሳካት አንጻር ክልሎች የሕዝብ ንቅናቄን ከመፍጠር ባሻገር ያላቸውን እምቅ የገቢ መሰብሰብ አቅም የሚያጠናክር እንደሆነም ገለጸዋል።

እንደ አፈ-ጉባዔ ካሳ ማብራሪያ ከ2005 በጀት ዓመት ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውለው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር አሁን ያለውን ቀመር ድክመቶች የሚፈታና አገሪቱ የደረሰችበትን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት የሚያደርግ ነው፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ የቀመሩ ዓላማ የክልሎችን እምቅ የገቢ መሰብሰብ አቅም፣ የሕዝብ ፍላጎት መዳሰስና የፊስካል ገቢያቸውን ማመጣጠን ነው ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ሕገ-መንግስታዊ መሠረት ያለውን የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ዝግጅትን በአግባቡ ለመከታተል፣ ለመምራትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠት በጉዳዩ ዙሪያ እውቀትና ግንዛቤ ሊኖር እንደሚገባም አብራርተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የምክር ቤቱን አባላት የማስፈጸም አቅም ለመገንባት የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።

ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና በመንግስት ፊስካል ሽግግር የአገሪቱን ተሞክሮና የሌሎች አገራትን ልምድ መነሻ በማድረግ የተሻለ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሲሆን፤ አዲስ በሚዘጋጀው የድጎማ ማከፋፈያ ቀመር ላይ መካተት በሚገባቸው ጉዳዮች፣ በቀመሩ ዓላማ፣ መርህና መስፈርቶች ላይ የምክር ቤቱ አባላትን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት እንዲያስችለው ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አፈ-ጉባዔ ካሳ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ስልጠና ላይ የኢትዮጵያ የፊሰካል/ ፋይናንስ ሽግግር ሥርዓት ተሞክሮ፣ ተግዳሮቶች፣ ውስንነቶችና የምንማራቸው ጠቃሚ ተሞክሮዎች፣ የፊስካል/ ፋይናንስ ሽግግር መርሆዎችና አግባቦች፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅም አለካክ መንገዶችና ዘዴዎች ዙሪያ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

እንዲሁም ፊስካል ፌዴራሊዝም ቀጥተኛና አግድሞሽ የፊስካል አለመመጣጠን በኢትዮጵያ፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ፣ የውጭ ፍላጎት ዳሰሳ/ አለካክ መንገዶች የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት መደረጉን ኢዜአን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።