ዩኒቨርሲቲው ከአውሮፓ ሕብረት የሶስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አገኘ

ሀዋሳ ጥቅምት 11/2004/ዋኢማ/– የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከአውሮፓ ሕብረት የሶስት ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ::

የዩኒቨርሲቲው የውጭና የሕዝብ ግንኙት ሃላፊ አቶ መልሰው ደጀኔ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ሕብረቱ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በዘጠኝ የአፍሪካ አገራት በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥምረት ለሚያካሂደው የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው::

ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ሊያገኝ የቻለው በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ በሚገኙት የኢራስመስ ዩኒቨርስቲዎች ማዕቀፍ ሥር በሚካሄደው የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓስፊክ የትምህርት ፕሮጀክት አካል በመሆኑ ነው ብለዋል ::

በፕሮግራሙ በኬኒያ የሚገኘውን የጆሞ ኬኒያታና በዩጋንዳ የሚገኘውን የማኬሬሬ ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ ከዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ የዩኒቨርሲቲው የውጭና የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ አቶ መልሰው ደጀኔ ገልጸዋል ::

ከዩኒቨርስቲዎቹ ጋር የሚካሄደው የትብብር ፕሮግራም ለ11 የድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች የሚያገለግሉ ሥርዓተ ትምህርቶችንና ሞጁሎችን በጋራ ማዘጋጀትን ጨምሮ የመምህራንና የተማሪዎች ልምድ ልውውጥን እንደሚያካትት አመልክተዋል::

የትብብር ፕሮግራሙ መካሄድ የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን አሠራርና ልምዶች በመጋራትና  የዩኒቨርስቲውን አቅም በማሳደግ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዲያገኝ ከማድረጉም በላይ በቀጣይ የተለያዩ የውጭ አገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እንደሚያስችለው ኃላፊው ተናግረዋል ::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ23ሺ በላይ ተማሪዎችን በቀንና በማታው የትምህርት መርሐ ግብር በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በ2004 ዓመተ ምህረት የትምህርት ዘመን ደግሞ ከ5ሺ በላይ አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።