የአፍሪካ ኅብረት የማዳጋሰካርን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማርገብ ያስተላለፈው ውሳኔ ገቢራዊ በመደረጉ ሁኔታዎች መሻሻላቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 11/2004/ዋኢማ/ – የአፍሪካ ኅብረት በማዳጋሰካር ተቀስቅሶ የነበረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማርገብ ያስተላለፈው ውሳኔ ገቢራዊ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ገለጸ፡፡

የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ዣን ፒንግ እንደገለጹት፤ ለማዳጋስካር ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔ ለመሻት ሕብረቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተንተርሶ የተወሰደው እርምጃ አዎንታዊና አበረታች ውጤት እያሳየ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ህገ መንግስታዊው ስርዓት ተመልሶ ገቢራዊ እየሆነ መምጣቱ ተቀባይነት እንዳለው ጠቁመው፤ በማዳጋስካር አዲስ ካቢኔና ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም እየተካሄደ ያለው የምክክር ስራም አርኪና በማላጋሲ ፓርቲዎች ባለፈው ወር አጋማሽ የተፈረመው ፍኖተ ካርታ ተከታዩ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም በተደረሰው የጋራ መግባባት መሰረት በቀጣይነት ገቢራዊ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸው እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግሩ ወቅት አክትሞ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ይህንኑ ጥረት አጥብቀው እንዲገፉበት አሳስበዋል፡፡

የደቡባዊ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በፖለቲካ ሕጋዊ ተቋምነቱ፣ በመከላከያና ደህንነት ትብብር የማዳጋስካር ፖለቲካዊ ቀውስ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ የተጫወተውን ሚናና ያላሰለስ ጥረት የሚያስመሰግነው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ለሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ህብረት ማንኛውንም ድጋፍ ወደፊትም እንደማያቋርጥ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የህብረቱ የሠላምና የጸጥታ ምክር ቤት ወደፊት ስብሳብ ለማካሄድ በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ዓለም ዓቀፋዊ የግንኙነት ቡድን ጋር በማዳጋስካር ጉዳይ ቀጣይ ስብሰባ እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡

ስብሰባው ዓለም ዓቀፉ ማህበረስብ የአፍሪካን ድጋፍ እንዲያግዝ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለአገሪቱ እንዲሰጥ ለማድረግ መሆኑን ኢዜአ ዘገባ መግለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።