ኮሚሽኑ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር ባካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት አስገኝቷል

አዲስ አባባ፤ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/ – የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር ባካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት ማግኘት መቻሉን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የዛሬ 10 አመት የተመሰረተ ሲሆን በነዚሁ አመታትም በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ ለመፍጠርና ሙስናን ለመዋጋት ሲሰራ መቆየቱም ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዲሱ ተስፋዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ሙስናን የሚጸየፍና በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ ለመፍጠር በተከናወነው መጠነ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰቡ መፍጠር ተችሏል።

ሙስና ለሀገር እድገት ማነቆ ስለመሆኑ ባለፉት 10 አመታት ከ5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማዳረሱን የገለጹት አቶ አዲሱ፤ ሙስናን የሚጸየፍ ዜጋ ከመፍጠር አንጻር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመስራት በመደበኛ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት መደረጉንም ተናግራዋል።

በተጨማሪም ከ200 በላይ የመንግስት ተቋማት የራሳቸውን የስነ-ምግባር ደንብ ያዘጋጁ ሲሆን፤ ለዚህም ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረጉንም አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

የመንግስት ተቋማት የሚያካሂዱትን የግዥ ስርዓት ህግና ደንብ የተከተለ እንዲሆን ተከታታይ የስነምግባር ትምህርት ሲያስተምሩ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ አዲሱ፣ ህግና ደንብን ጥሰው የተከናወኑና ተወዳዳሪዎችን እኩል ያላሳተፉ የጨረታና የግዥ ሂደቶች እንዲታገዱ መደረጉንም አመልክተዋል።

የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ከወጣ በኋላ የሀገሪቱን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ 22ሺ ተሿሚዎችና በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ንብረታቸውን ማስመዝገባቸውን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በቀጣይ የሃብት ምዝገባው ስራው ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ቀጣይ የኮሚሽኑን የትኩረት አቅጣጫ የተለየ ሲሆን፤ እነዚህም የሀገሪቱን እድገት በሚያደናቅፉ የሙስና ዓይነቶች፣ የመንግስት ግብርና ታክስ አሰባሰብ፣ የመንግስት ግዥና ሽያጭ ስርዓትና የመልካም አስተዳደር ናቸው።

ኮሚሽኑ ላቀደው እቅድ ስኬት የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ መተኪያ የለውም ያሉት አቶ አዲሱ በቀጣይም ራሱን ከሙስና በማራቅና ማንኛውም የሙስና ተግባር ሲፈጸም ከተመለከተ ለኮሚሽኑ ጥቆማ እንዲያደርስ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋልታ የኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ