የቤት ሰራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች ራሳቸውን ከኤችአይቪ እንዲጠብቁ የሚያስችል ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/ – የቤት ሰራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች ነጭ ጋዝ ለመግዛት ወደ ማደያ በሚሄዱበት ወቅት ራሳቸውን ከኤችአይቪ/ኤድስ እንዲጠብቁ ለማስቻል ስለኮንዶም የማስተዋወቅ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለፀ።

የኮንዶም ማስተዋወቅ ስራው የሚያካሄደው ዲኬቲ ኢትዮጵያ፣ ቶታል ኢትዮጵያና ቢዝነስ ኮኦሊሽን አጌነስት ኤችአይቪ/ኤድስ በጋራ በመሆን “ኮንዶምና ኬሮሲን” በተሰኘ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው።

“ኮንዶምና ኬሮሲን” የተሰኘው ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ከሁለት ዓመታት በፊት በአንድ የቶታል ነዳጅ ማደያ ውስጥ ለ60 ቀናት የተካሄደ ሲሆን፤ አሁን የተጀመረውም በአምስት የቶታል ነዳጅ ማደያ ውስጥ ለአንድ መቶ ቀናት እንደሚሆንም ተገልጿል።

የሚከፈቱትም በተመረጡ አምስት የቶታል ማደያዎች ማለትም በቅሎ ቤት፣ ሰባተኛ፣ መሳለሚያ፣ ላምበረትና አዲሱ ገበያ አካባቢ ባሉ የቶታል ማደያዎች ሲሆን፤ ስለኮንዶም አጠቃቀም ትምህርት ይሰጣል።

የ“ኮንዶም እና ኬሮሲን” የተሰኘው ፕሮጀክት ባለፈው ጥቅምት 14 መርካቶ ሰባተኛ አካባቢ በሚገኘው የቶታል ማደያ አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩን በማስመልከት የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ መካሄዱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።