በሪዮ የዘላቂ ልማት ጉባዔ የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት አፍሪካውያን በጋራ እንዲቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠየቁ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/– ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሪዮ ከተማ በሚካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የዘላቂ ልማት ጉባዔ የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት አፍሪካውያን በጋራ መቆም እንዳለባቸው አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨው ግንቦት ወር በሪዮ ዲጄኔሪዮ ከተማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ የአፍሪካ አቋም ምን ሊሆን እንደሚገባው የሚመክረውን የሚኒስትሮች ጉባዔ አዲስ አበባ ውስጥ ሲከፍቱ እንደተናገሩት በአህጉሪቷ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አፍሪካውያን በጉባዔው በጋራ ድምጻቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከ20 ዓመት በፊት የዓለም መሪዎች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን አጀንዳ 21ን በማጽደቅ አስፈላጊ የሃብትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያሳዩ እምነት ተጥሎ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ20 ዓመታት በኋላ መሪዎቹ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ከዓለም ለውጡ ጋር ያልተስተካከለ ምጣኔ ሃብትና ቴክኖሎጂ ባላቸው እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ዘለቄታዊ ልማት ማረጋገጥ ፈታኝ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ታላላቅ ጉባዔዎች የዓለም መሪዎች በርካታ ቃል ቢገቡም ቃላቸውን ጠብቀው በተጨባጭ ተግባራዊ አለማድረጋቸው አፍሪካውያንን ተስፋ ሳያስቆርጥ ለበለጠ ትግል ድምፃቸውን በጋራ ማሰማት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በጉባዔው የአፍሪካን ተደራዳሪነት በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ ውጤታማና ትክክለኛ ስትራቴጂዎችን መንደፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልጸዋል፡፡

በሪዮ ዲጄኔሪዮ ጉባዔ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉት የሪፓብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሴሶ ንጌሶ በበኩላቸው ጉባዔው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አፍሪካውያንም የአህጉሪቱን ድምጽ ወጥ በሆነ መልኩ በጉባዔው ለማንጸባረቅ በጥልቀት መክረው የጋራ አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን ይህን ማድረግ ከቻሉ አፍሪካ በጉባዔው ትክክለኛና የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ የሚያስችላት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ፈተና የተጋረጠበት ቢሆንም አፍሪካውያን የፖለቲካ መሪዎች በብሔራዊና ቀጣናዊ አጀንዳቸው ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባም አስምረውበታል፡፡

ይህም ዘላቂ ልማትን በአፍሪካ ለማረጋገጥ የሚደረገውን የተደራዳሪነት አቅም እንደሚያጎለብተው አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ጃን ፒንግ በዚሁ ወቅት ባሳሙት ንግግር ባለፈው ሐምሌ ወር በኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቡ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪካ ርዕሳነ ብሔራት ጉባዔ ላይ በሪዮ የዘላቂ ልማት ጉባዔ አፍሪካ በጋራ ድምጽ እንድትወከል መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡

በጉባዔው የአፍሪካን ጥቅም የሚያንጸባርቅና የሚያስጠብቅ ድምጽ ለማሰማት ጠንካራ የጋራ አቋም መያዝ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት በተካሄደው የአፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባዔ በቅርቡ በሞት የተለዩትን ኬንያዊ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ፕሮፌሰር ዋንጋሪ ማታይን ለማስታወስ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡

በጉባዔው ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የተወከሉ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸውንም የኢዜአን መዘገቡን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጠቁሟል።