በክልሉ ክረምትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል

ሀዋሳ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ::

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው በክልሉ ከክረምት ዝናብ ማብቃት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ አስቀድሞ ለመከላከል የአልጋ አጎበሮች ሥርጭትና የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል::

ቢሮው ካለፈው የሐምሌ ወር ጀምሮ 525 ሺ 177 የአልጋ አጎበሮችን ማሠራጨቱን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ ገልጸዋል::

ባለሙያው እንዳሉት አጎበሮቹ የተሠራጩት በክልሉ ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ በ1 ሺ 356 የገጠር ቀበሌዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ነው::

ከአጎበር ሥርጭቱ በተጨማሪ በ653 ሺ 733 የመኖሪያ ቤቶች ላይ 2ሺ 521 ሊትር የፀረ- ወባ ኬሚካል ርጭት መከናወኑን  የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው  ገልጸዋል::

የአጎበር ዕደላውና የኬሚካል ርጭቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ እንደሚያስችል ባለሙያው አመልክተዋል::

በተጨማሪም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በተካሄደ የሕብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ በርካታ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ሥራዎች መከናወናቸውን ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።