በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ያለው የሁለትዬሽ ግንኙነት እጅግ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል- ዶናልድ ካቤሩካ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2004/ ዋኢማ/ – በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ያለው የሁለትዬሽ ግንኙነት እጅግ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዶናልድ ካቤሩካ ገለጹ።

ዶክተር ዶናልድ ካቤሩካ አዲስ አበባ ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተዋያይተዋል።

ሚስተር ካቤሩካ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በብድርና በልማት እርዳታ መልክ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለአብነትም በሃይል ተቋማት ግንባታ፣ በሃይል ማስተላለፍ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ለሚደረጉ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ዶናልድ ካቤሩካ እንደጠቀሱት የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋሮች ከሚባሉት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ባንኩ ወደፊትም ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ እንዲሚቀጥል አስረድተዋል።

ሚስተር ካቤሩካ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር በነበራቸው ቆይታም ህዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ በፈረንሳይ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል አገራት ጉባኤና በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ታህሳስ ወር ላይ በሚካሄደው የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በተመለከተ የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ላይ ባንኩ እያደረገ ስላለው ጠንካራ ድጋፍ አመስግነዋል።

በአለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በተደረጉት ድርድሮች የተገኙትን ውጤቶች ጠብቆ ለመጓዝና ወደፊትም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ጥረት እንደሚደረግም አቶ መለስ ገልፀዋል።

አፍሪካ በጉባኤው ላይ ተደማጭ ለመሆንና በሚካሄዱት ድርድሮች የተሻለ ውጤት ለማመጣት በአንድ ድምጽ መስራት ይኖርበታልም ብለዋል።

አፍሪካ በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በተቋም ደረጃ መወከል ስለምትችልበት ሁኔታም የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በደርባኑ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፈው የልኡካን ቡድን መሪና ዋነኛ ተደራዳሪ ናቸው።