የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከአምስት ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲሰ አበባ፤ ህዳር 4/2004/ ዋኢማ/- የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኅብረቱን አገናኝ ጽህፈት ቤቶች ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት በሳምንቱ መጠናቀቂያ ላይ ከአምስት ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ተፈራረመ፡፡

ኮሚሽኑ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ስምምነቱን ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዲን፣ እንግሊዝና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተፈራርሟል፡፡

የኮሚሽኑ አገናኝ ጽህፈት ቤቶች በኅብረቱ የተለያዩ አባል አገራት ዘላቂ ሠላምና ፀጥታ እንዲጎለብት የሚያካሂዱትን ጥረት የሚያገዝ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ያሉትንና ወደፊት የሚከፍታቸውን አዳዲስ አገናኝ ጽህፈት ቤቶች ከአጋሮች ጋር በመሆን በሚገባና ቀጣይነት ባለው መልኩ በገንዘብ ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት እ.ኤ.አ በ2009 መፈራረሙን በመግለጫው ተጠቀሷል፡፡

ሰሞኑን የተደረሰው ስምምነትም የዚሁ ቀጣይ አካልና ሁለተኛው ምዕራፍ እንደሆነ ነው የኮሚሽኑ መግለጫ ያስረዳል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሠላምና ፀጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ራምታኔ ላማምራ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አጋር አገሮች ለኮሚሽኑ አገናኝ ጽህፈት ቤቶች የሚያደረጉትን የገንዘብ ድጋፍ ለመቀጠል መስማማታቸውን አወድሰዋል፡፡

አጋር አገሮችም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በአህጉሪቷ ሠላምና ጸጥታን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት በቅርበት እንደሚደግፉ ዳግም ማረጋገጣቸውን መግለጫውን ጠቅሶ፤ የአፍሪካ ኅብረት በአሁኑ ወቅት በ11 የአፍሪካ አገራት 11 አገናኝ ጽህፈት ቤቶች እንዳሉት ኢዜአ ዘግቧል፡፡