አንዳንድ ነጋዴዎች የስኳር አቅርቦት የለም በሚል ሰበብ ስኳርን ማከማቸት መጀመራቸው አግባብነት የሌለው መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2004/ዋኢማ/ አንዳንድ ነጋዴዎች የስኳር ዋጋ ይጨምራል፣ አቅርቦቱም የለም በሚል ሰበብ ስኳርን ማከማቸት መጀመራቸው አግባብነት የሌለው መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰሞኑን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ፤ በስኳር ኮርፖሬሽን ከ600 ሺ ኩንታል በላይ የስኳር ምርት በክምችት መኖሩንና ምንም አይነት የስኳር እጥረት እንደሌለ ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ፤ መንግስት በሀገሪቱ የስኳር እጥረት እንዳይፈጠር በተለያየ ወቅት ገበያውን የማረጋጋት ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት በስኳር ኮርፖሬሽን ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የስኳር ክምችት ከመኖሩም በላይ  መተሀራ፣ወንጂና ፊንጫ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው በማምረት ላይ ስለሚገኙ የአቅርቦት ችግር ፈጽሞ እንደለሌ ተገልጿል።

በመሆኑም የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራትና ነጋዴዎች የስኳር ማከፋፈሉን ተግባር በመቀጠል ሸማቹን ህብረተሰብ በቅንነት ማገልገል ይገባል፡፡

ሸማቾችም ስኳርን በችርቻሮ መደብሮች የማያገኙ ከሆነ በአቅራቢያው ከሚገኙት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች ወይም ከኢትፍሩት የመሸጫ ሱቆች መግዛት የሚችል መሆኑን መግለጫው ማስታወቁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ
አዓ