ፕሬዚዳንት ግርማ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል የቦርድ ሊቀ መንበር ዶክተር ሮበርት ኤፍ ዋልተርንን አነጋገሩ

አዲስ አበባ, ህዳር 15 ቀን 2004 (ዋኢማ) – ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ሮበርት ኤፍ ዋልተርንን ትላንትና በፅህፈታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በጎንደርና በአዋሳ ዩኒቨርስቲዎች ትራኮማን ለማጥፋት ህክምናና ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝና ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ግርማ መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት አንድ የመንግሥት ባለስልጣን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም ድርጅቱ ለሚያከናውነው ተግባር የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ፕሬዚዳንት ግርማ አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማውጣት ቃል መግባቱንም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም 99 ሚሊዮን ዶላር ለትራኮማ ህክምና የሚያገለግል መድሃኒት እንደሚያቀርብም አስረድተዋል፡፡

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ሊቀመንበር ዶክተር ሮበርት ኤፍ ዋልተርን እንዳሉት ድርጅቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግሥት አመቺ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ 11 ሚሊዮን ህጻናት በትራኮማ በሽታ እየተጠቁ መሆኑንና ችግሩን ለማስወገድ ድርጅቱ በሙሉ ዓቅሙ እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል፡፡(ኢዜአ)