የሙያ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና የስነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሕገ-መንግስቱን በማስተዋወቅ በኩል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ ህዳር 15/2004/ዋኢማ/– የሙያ ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የስነ- ጥበብ ባለሙያዎች ህገ-መንግስቱን ለህብረተሰቡ ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አስታወቁ።

አፈ-ጉባዔው አቶ ካሳ ተክለብርሃን ይህን ያሳሰቡት ዛሬ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሙያ ማህበራት፣ ለመገናኛና ለስነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ብሔራዊ ኮንፈረንስ በንግግር ሲከፍቱ ነው።

የመገናኛ ብዙሃንና የስነ-ጥበብ ባለሙያዎቻች ሙያቸውንና በእጃቸው ላይ ያለውን የሃገርና የህዝብ ሃብት የሆነውን እሴት በአግባቡና በኃላፊነት ከተጠቀሙት ከድህነት ማምለጥ  እንደሚቻል አፈ-ጉባዔው አሳስበዋል።

ምክር ቤቱም ባለፉት አመታት ህገ-መንግስቱን ከማስተዋወቅ አንፃር ከፈፀማቸው ተግባራት ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን አስተምህሮት፣ የፊት ለፊት ውይይቶችና የህገ-መንግስቱን ቅጂዎች እያባዙ የማሰራጨት ተግባራት በሙከራ ደረጃ የሚታዩ ስራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ህገ-መንግስቱን ለመላ ዜጐች ለማዳረስ፣ ለማስተዋወቅና ለማስተማር ኃላፊነት ይዞ በተንቀሳቀሰባቸው አመታት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ጅምር ሊባል የሚችል ሙከራ ማድረጉን ገልፀዋል።

የዜጐችን የዕለት ተዕለት ህይወት ከምናባዊ አለም ጋር በማዋሃድ በተግባራዊ እርምጃቸው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ካለው የስነ-ጥበብ ዘርፍ ጋር ግን ታቅዶ በሙከራ ደረጃም ቢሆን ህገ-መንግስቱን የማስተዋወቅ፣ የማስተማርና የማስረፅ ስራ ሰርተናል ማለት አይቻልም ብለዋል።
በመሆኑም ህገ-መንግስቱን በማስተዋወቅና በማስተማር ረገድ እስካሁን በተፈፀሙ ተግባራት ዙሪያ የታየው የተደራሽነትና የጥራት ጉድለት በህዝቡና በባለሙያው ዘንድ ለዘመናት ነግሰው ከቆዩት የባህልና የአመለካከት ችግሮች ጋር ሲደመር የመላ ዜጐችን ህገ-መንግስታዊ እውቀት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጐታል ተብሎ እንደሚታመን አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል።

በመሆኑም የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአል የህገ-መንግስቱን ዋና ዋና እሴቶች በማስተዋወቅ እንዲከበር የተወሰነው በማለት ገልፀዋል።

በኮንፈረንሱ ላይም የሕገ መንግስት መርሆዎች በሚል የመገናኛ ብዙሃንና የስነ-ጥበብ የሕግ ማዕቀፎች፣ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትና የኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ሕገመንግስታዊ እሴቶችና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ይዘቶች ብዙሃነትን ከመንፀባረቅ አንፃርና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ውይይቱ እንደሚካሄድ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።