ረቂቅ ሞዴል ደንቡ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ልማቱን ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3 ቀን 2004 /ዋኢማ/ – የሊዝ ዓዋጁን ለማስፈፀም የተዘጋጀው ረቂቅ ሞዴል ደንብ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥና ልማቱን ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ረቂቅ ደንቡ በዓዋጁ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ብዥታ የሚያጠራ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በረቂቅ ደንቡ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ሲካሄድ እንዳሉት በአገሪቷ የተጀመረው ፈጣን ልማት ቀጣይነት የሚኖረው መሬት የሕዝብና የመንግሥት መሆን ሲችል ነው፡፡

በአገሪቷ ከሚመዘገበው የልማት ትሩፋትም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሕዝብና የመንግሥት ኃብት የሆነውን መሬት አጠቃቀሙን ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመሬት አጠቃቀም ሥርዓቱን ፈር ለማስያዝም በዓዋጅ የተደገፈ አዲስ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ የወጣው የሊዝ ዓዋጅ 721/2004 ተፈጻሚ ለማድረግ የረቀቀው ሞዴል ደንብም የሕዝብ የላቀ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ልማቱን በሚያስቀጥል አኳሃን መዘጋጀቱን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡

ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ደንብ ኅብረተሰቡ በሊዝ ዓዋጁ ላይ የነበረውን ብዥታ የሚያጠራ ከመሆኑም ባሻገር፤ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግራዝማች በለጠ መንገሻ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ረቂቅ ደንቡ በዓዋጁ በግልጽ ያልተብራሩትን ጉዳዮች በዝርዝር ያብራራ ነው፡፡

ይህም ቀደም ሲል በወጣው የሊዝ ዓዋጅ 721/2004 ላይ ኅብረተሰቡ ይዞት የነበረውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያጠራ መልካም ዕድል ፈጥሮለታል ብለዋል፡፡

ነገር ግን አሁን በተጨባጭ እየታየ ያለው አሰራር የመሬት ግብርን ወደኋላ ተመልሶ የዓመታት ውዝፍ የሚያስከፍል በመሆኑ የመሬት ግብር አከፋፈሉ ይህ አዓዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይገባል የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

በተመሳሳይም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው መንግሥት ያወጣው ረቂቅ ሞዴል ደንብ ዓዋጁ ላይ ጠቅለል ብለው የተቀመጡት ጉዳዮች በማብራራት ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚያደርግ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተለይ አዋጁ በአገሪቱ የሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ቤት የሌላቸውን ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ረቂቅ ደንቡ የነገሰውን ብዥታና ሕዝቡ አድሮበት የነበረውን ስጋት ገላልጦ የዓዋጁን መንፈስ በውል እንዲገነዘብ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ያም ሆኖ ነባር ይዞታ ሲሸጥ ወደ ሊዝ ይገባል የሚለውን አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 3 በረቂቅ ደንቡ ላይም በስፋት ያልተብራራ በመሆኑ ጉዳዩ ዳግም ቢጤን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከአሥሩ ክፍለ ከተሞች የተወከሉ ነዋሪዎች በተሳተፉበት በዚሁ ውይይት ላይ በአብዛኛው በነባር የመሬት ይዞታና የሊዝ ክፍያ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ ለአቶ መኩሪያ ኃይሌ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የሚወጡት ዓዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአፈጻጸም ማኑዋሎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ እንዲፈጥርና እነዚህን በአግባቡ በማስፈጸም በኩል በአስፈጻሚዎች የሚታዩ ድክመቶችን ለማስወገድ የፈጻሚዎችን አቅም ማብቃት ላይ እንዲተኮር ከተሳታፊዎች ጥያቄ ቀርቧል፡፡

አቶ መኩሪያ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ እንዳሉት የሊዝ ክፍያ መነሻን በተመለከተ በቀጣይነት በሚወጣው መመሪያና የአፈጻጸም ማኑዋል ላይ በዝርዝር የሚገልጽ ይሆናል፡፡

ነባር ይዞታን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓዋጅ የወጣው በ1986 ሲሆን፣ ቀጥሎ በ1994 የመጨረሻው ደግሞ በ2004 የወጣው የሊዝ ዓዋጅ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ነባር ይዞታዎች ለልማት ማነቆ ናቸው የሚል እምነት በመንግሥት በኩል አለመኖሩን ሚኒስትሩ አመልከተው፣ ነባር ይዞታን በተመለከተ በሕዝቡ በኩል ያለው ቅሬታ መንግሥት ተገንዝቦ ለጉዳዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

አሉ የተባሉትን ቅሬታዎችን እልባት ለመስጠትም መንግሥት ከነባር ይዞታ ባለቤቶች ጋር ምክክር እንደሚያካሂድ አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የመሬት ግብርን ዓዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንጂ ወደኋላ ሄዶና ኪራይና ሊዝን ደርቦ ማስከፈል ሕገ-ወጥ ድርጊት መሆኑን በማስመር የዚህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽም አካል ካለ ተገቢው እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል፡፡

ዓዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአፈጻጸም ማኑዋሎችም ድረ-ገጽን ጨምሮ ለሕዝቡ ተደራሽ የሚደረግበትን አሰራር እንደሚዘረጋ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

የከተማ ቦታን በሊዝ ለማስተዳደር እንዲያስችል የተዘጋጀው ይኸው ረቂቅ ሞዴል ደንብ ከተሳታፊዎች የተገኘውን ገንቢ ግብዓት በማካተት በክልሎች አሊያም በከተማ አስተዳደር ካቢኔ ጸድቆ ገቢራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የሊዝ ዓዋጅ አገሪቱ ከምትከተለው የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ የመሬት አሰጣጥ ሥርዓት የመጠቀም፣ የመጠቀም መብትን በሊዝ የማስተላለፍ መብትን በግልጽ የሚለይ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ማጣቀሻዎች እንደሚያመላክቱ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡