የእምነት ተቋማት ለዘመናት የቆየውን የመቻቻል ባህል አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ

ድሬዳዋ ፣ ጥቅምት 6/2006 (ዋኢማ) – በድሬደዋ ከተማ የሚገኙ የእምነት ተቋማት ለረጅም ዘመናት የቆየውን የመቻቻል ባህል አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው የከተማው ምክትል ከንቲባ አሳሰቡ፡፡

 

ምክትል ከንቲባ አቶ አደም ፋራህ በትላንትናው ዕለት ለ1ሺ 434ኛ ጊዜ የተከበረውን የኢድ አል አድሀ/አረፋ/ በዓል አስመልክቶ እንደገለጹት የሁሉም ሀይማኖቶች መርህ ሰላም፣ ፍቅርና መከባበር ነው፡፡

 

ሀይማኖት በምንም መልኩ ግጭትና ብጥብጥን የማይደግፍ እንደሆነ የገለፁት ምክትል ከንቲባው በሀይማኖት ሽፋን ድብቅ አጀንዳቸውን ለማራመድ የሚፈልጉ ሀይሎች የሚያደርጉት ጥረት ሊወገዝ የሚገባ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

አገሪቱ በተያያዘችው የዕድገትና የልማት ጉዞ በርካታ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ባለችበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ያወሱት አቶ አደም አስተዳደሩ በልማትና መልካም አስተዳደር የያዘውን ግቦች ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የድሬዳዋ እስላማዊ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ አቶ ኡስታዝ አዩብ ሀሰን በበኩላቸው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለተቸገሩ በመርዳትና ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በመሆን በዓሉን ሊያከብር ይገባል ብለዋል፡፡

 

ህብረተሰቡ የመቻቻልና የአብሮነት ባህሉንም ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አቶ ኡስታዝ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡