መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 7/2006 (ዋኢማ) – መንግስት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር   በሚግባባቸው ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ በሕዝብ  ተወካዮች  ምክር  ቤት ተገኝተው የመንግስት እቅድ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት መንግስት በሰላማዊ መንገድና ሕግን  ተከትለው  ከሚንቀሳቀሱ  ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት  ዝግጁ  ነው።
መንግስት ሁልጊዜም በመወያያት እንደሚያምን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገ መንግሰቱን አክብረው ከማይንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋራ ተባብሮ ለመስራት ግን ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል። 
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ስለታሰሩ ግለሰቦች በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ማንኛውም በሽብርና በሙስና የተጠረጠረ ግለሰቦች በአገሪቱ ሕግ መሠረት ምንም ይቅርታ እንደማይደረግላቸው አብራርተዋል። 
የሐይማኖት መብታችን ይከበር ብለው  ለጠየቁ ዜጎች  በግልፅ  የሐይማኖት ተወካዮቻቸውን በመምረጣቸው መብታቸው መከበሩን የጠቀሱት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ  ሌላ አጀንዳ የሚያረምዱት ጉዳያቸው በሕግ እንደሚታይ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የምዕት ዓመቱን ግቦች ለማሳካት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ  ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የቻለች አገር መሆኗን የጠቆሙት  ክቡር  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ11 ዓመታት የሁለት  አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የግብርና ምርቶችን ለማሳደግና የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ሥራዎችን  ለማከናወን  አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ  በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲንቀሳቀስ መቆቱን የገለጹት ክቡር  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በሚሊዮን  ሄክታሮች የሚቆጠር መሬት ላይ የአነስተኛ የመስኖ ልማት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።
በኢንዱስትሪ  ክፍለ ኢኮኖሚው ላይ ለሚሠማሩ  ባለሃብቶች  መንግሥት ከመሬት ጀምሮ የኢንዱስትሪ ዞን በማዘጋጀትና ልዩ ልዩ ድጋፎችን  እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ምርቱ  ላይ እሴት የሚጨምሩ ምርቶች ላይ የተሰማሩት ባለሃብቶች  ይበረታታሉ ብለዋል ። 
መንግሥት በ2006 ዓም ከወጪ ንግድ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ 2005 ዓ. ም 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት  በዕቅድ  ተይዞ   የግብርና ምርቶች ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት 3 ቢሊዮን  ዶላር ብቻ መገኘቱን  አስረድተዋል ።
የቤቶች  ልማት እስካሁን 280 ሺ ቤቶች  ተገንብተዋል ያሉት  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለወደፊቱ  የቤቶች  ግንባታን ለማፋጠን  የግንባታ ግብዓቶችን  የሚያመርቱ  የውጭ  ኩባንያዎች  ወደ  ሃገር ውስጥ  እንዲገቡ እየተደረገ  ነው ብለዋል ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክቡር ፕሬዝዳንቱ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን በአንድ ተቃውሞና በሙሉ ድምፅ  ድጋፍ  መፅደቁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።