አምራቾችና የንግድ ድርጅቶች በዓለም ዓቀፉ የንግድ ሥርዓት ላይ በቂ እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 8/ 2006 (ዋኢማ) -አገር በቀል አምራቾችና የንግድ ድርጅቶች በብሄራዊና አለማቀፋዊ ደረጃ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጠናከር በዓለም ዓቀፉ የንግድ ሥርዓት ላይ በቂ እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 

ከዓለም አቀፉ ተሞክሮ በተወሰዱ በአስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ማስፈጸም እና የቴክኒክ ደንቦች ማስተባበርና የህጋዊ ስነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ትላንት በአፍሮ ዳይት ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሂዷል።

 

በሚኒስቴሩ የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ አሊ ሲራጅ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ንግድ አካል በመሆኗ አገር በቀል አምራቾችና የንግድ ድርጅቶች በብሄራዊና አለማቀፋዊ ደረጃ የሚገጥማቸውን ውድድር በአሸናፊነት ለመወጣት አቅማቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪነታቸውን ማጠናከር ይገባል።

 

ይህንን ለማሳካት በዘርፉ ያሉ ተዋናዮች ራሳቸውን ከዓለም አቀፉ ስርዓቱና ተወዳዳሪነት ላይ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውድድር በማድረግ ሲችሉ እንዲሁም ቀጣይና አስተማማኝ ገበያ ሲያገኙና አቅማቸውን ሲገነቡ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ ከዓለም ዓቀፉ የንግድ ስርዓቱ ላይ የተሻለ ልምድን መቅሰምና ህጎችን ማሻሻልና መተግበር እንደሚያስፈልግ አቶ አሊ አስረድተዋል።
ከዓለም አቀፉ ተሞክሮ የተወሰዱት አዋጆች ዋና አላማም የአገራችን የግብይት ሥርዓት የመወዳደሪያ ሜዳው ለሁሉም የግብይቱ ተዋናይ እኩል በማድረግ ተወዳዳሪነትን ለማበረታታት፣ የንግዱ ማህበረሰብ በተጠያቂነትና በሃላፊነት እንዲሰራ ለማድረግና የሸማቹን መብት ጥቅምና ደህንነት ለማሰከበር መሆኑን ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ማሞ በበኩላቸው አዋጁ የወጣው በንግድ ልውውጥ ላይ የሚውሉ የመለኪያ መሳሪያዎችና የታሸጉ የንግድ ዕቃዎች ወደ ገበያ ከመግባታቸው በፊት ትክክለኛነታቸውን የሚረጋገጥበትን ሥርዓት በመዘርጋት ሸማቾች ለሚከፍሉት ዋጋ የተመጣጠነ የንግድ ዕቃና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተጨማሪም አዋጁ ከጤና፣ ከደህንነትና አካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ጤንነት፤ ደህንነትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎችን መጠበቅና እንዲሁም የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የክትትል ሥራ እንዲያካሂዱ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
በውይይቱ ወቅት ከተሳተፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል።