ኤጀንሲው ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃዶችን ለመስጠት አቅዷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በተያዘዉ በጀት ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃዶችን ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው የበጀት ዓመት እቅድ እንደሚያሳየው ግምታዊ የኢንቨስትመንት ካፒታላቸው 129 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለሚሆኑ 1 ሺህ 5 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፍቃድ ለመስጠት መታቀዱን የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

እቅዱ ከባለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር 165 በመቶ እድገት እንደሚያሳይ ነው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በማስመዝገብ ላይ ባለችው ፈጣንና ተከታታይ የምጣኔ ሃብት እድገትና ባለሃብቶችን ለመሳብ ባስቀመጠቻቸው ምቹ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ምክንያት ተመራጭ የኢንቨንስትመንት መዳረሻ አገር እየሆነች መጥታለች፡፡

እንደ አቶ ጌታሁን ገለፃ በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ 264 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ምርትና አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡