በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመረጃ መረብ ሊገናኙ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 8/ 2006 (ዋኢማ) – በተያዘው የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመረጃ መረብ (በስኩልኔት ፕሮግራም) እንደሚገናኙ የከተማው ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

 

የቢሮው ሃላፊ አቶ ዴላሞ ኦቶሪ ለዋልታ እንደገለጹት ት/ቤቶቹን በመረጃ መረብ ለማስተሳሰርና የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ በ23 ሚሊዮን ብር ወጪ የ2ሺ 500 ኮምፒውተሮች ግዠ ተፈፅሟል።

 

ፕሮግራሙ በሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን እርስ በርስ መረጃና ልምድ በመለዋወጥ ለትምህርት ጥራትና ለመማር ማስተማሩ ሥራ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

 

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች በስነ ምግባር የታነፁና ከደባል ሱሶች ነጻ እንዲሁም ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ  እንደሚገኝ አቶ ዴላሞ ተናግረዋል።

 

በ2005 ዓ.ም  በየትኛውም  የትምህርት  ቤቶች  አካባቢ መጠጥ ቤቶች ፤ ሺሻ ቤቶችና ጫት ቤቶች  እንዲነሱ የሚያዝ  ደንብ  ተዘጋጅቶ በኢዲስ  አበባ ምክርቤት  መጽደቁን  አቶ ዴላሞ አስታውሰዋል፡፡

 

በከተማዋ በተደረገ ጥናት ችግር ያለባቸው 47 ትምህርት ቤቶች መለየታቸውንና በተያዘው የትምህርት ዘመንም የትምህርት ቤቶቹን አካባቢዎች ለማሻሻል እርምጃ እንደሚወሰድ ሃላፊው ገልጸዋል ።

 

የትምህርት ጥራት  ለማሻሻል  የመምህራን ብቃት ወሳኝ እንደሆነ የጠቀሱት  አቶ ዴላሞ   ብዛት  ያላቸው መምህራን በዲግሪና በማስተርስ  ዲግሪ  እንዲመረቁ  በማድረግ  ከ5ኛ  ክፍል  ጀምሮ ዲግሪ ያላቸው መምህራን በመሰናዶ ትምህርት ደግሞ ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው መምህራን እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል ።

 

በዘንድሮ የበጀት ዓመት ሁሉም  ተማሪዎች ከ 50 በመቶ በላይ ውጤት እንዲያመጡ  ዕቅድ  መያዙን የጠቆሙት አቶ ዴላሞ በከተማዋ በ12ኛ ክፍል ፈተና ጥሩ ውጤት  የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች  ቁጥራችው እያደገ  መምጣቱን  አያይዘው  ተናግረዋል ።

 

በአዲስ   አበባ  ከተማ   የአፀደ ህፃናት የትምህርት  ሽፋን  93 ነጥብ 5 ፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን  105  በመቶ መድረሱንና   የሁለተኛ  ደረጃ የትምህርት  ሽፋን  80 በመቶ መሆኑን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል