ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የጃፓኑን ጠቅላይ ሚኒስትርን አነጋገሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2006 (ዋኢማ) – ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የጃፓኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤን በብሄራዊ ቤተ-መንግስት ተቀብለው አነጋገሩ።

ሁለቱ ከፍተኛ ባልስልጣናት የየአገሮቻቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጃፓን በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረገች ላለው ጠንካራ የልማት ድጋፍ አመስግነዋል።

ለረዥም አመታት የዘለቀው የኢትዮ-ጃፓን የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት በኢንቨስትመንትና ንግድ ረገድም የበለጠ እንዲጠናከር ዶክተር ሙላቱ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤ በበኩላቸው የኢትዮ-ጃፓን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት በእጥፍ ለማሳደግ መንግስታቸው አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የመሪዎችን ውይይት የተከታተሉት በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ሁለቱ ባለስልጣናት በአብዛኛው በሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት የትብብር ጉዳዮች ላይ በሰፊው መነጋገራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃፓን መንግስት ድጋፍ በ1950ዎቹ የተሰራውንና በብሄራዊ ቤተ-መንግስት ቅጽር ግቢ የሚገኘውን የጃፓን መናፈሻ ከባለቤታቸውና ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በመሆን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

መናፈሻው እኤአ በ1956 ቀዳማዊ ሃይለስለሴ በጃፓን ይፋዊ የስራ ጉብኘት አድርገው ከተመለሱ በኋላ የተገነባ ነው።

እኤአ በ1960 የጃፓን አልጋ ወራሽ ልዑል አኪሂቶና ባለቤታቸው የመናፈሻ ስፍራውን መጎብኘታቸው ተጠቅሷል።

እንደ ኢዜአ  ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀው በዛሬው እለት ወደ አገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።