የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የነመላኩን ጉዳይ የማየት ስልጣን እንዳለው በየነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2006 (ዋኢማ) – የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱትን የነመላኩ ፈንታን ጉዳይ የማየት ስልጣን እንዳለው ብይን ሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ብይኑን የሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በታህሳስ 24፣ 2006 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ያሳለፈውን የህገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ በመመርኮዝ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ትላንት ከሰዓት በዋለው ችሎት አሳውቋል፡፡
ምክር ቤቱ በሁለት አዋጆች ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ሁለት አንቀጾች ከህገ መንግስት ጋር ስለሚፃረሩ ተፈፃሚነት ሊኖራቸው አይገባም የሚለውን የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ውሳኔ በከፍተኛ ድምፅ ያፀደቀው፡፡ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8 (1) እና የአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7 (1) በስራቸው ምክንያት የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳይ የማየት ስልጣን ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው የሚል ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡
ሆኖም የምክር ቤቱ ውሳኔ እነዚህ አንቀጾች ህገ መንግስቱ ውስጥ ካሉ የተከሳሽ ይግባኝ የማግኘት መብት እና ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው ከሚሉ መርሆች ጋር ይጣረሳሉ በሚል ተፈፃሚ እንዳይሆኑ ተደርገዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ትላንት የተሰየመው የከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት የነመላኩ ፈንታን ጉዳይ የማየት ስልጣን እንዳለው ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም የቅድመ ክስ ክርክር ማድረግ ሳያስፈልግ ወደ መደበኛ ክርክር እንዲገባ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤያን ህግ የተመሰረተው ክስ ዝርዝር ላይ መቃወሚያ ማቅረብ እንገልጋለን በማለታቸው ፍርድ ቤቱ መቃወሚያቸውን ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 29፣ 2006 ይዟል፡፡
በዚሁ ወቅትም የኮሚሽኑ ዐቃቤያን ህግ ያልቀረቡ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ በማድረግ እንዲቀርቡ ጥሪ እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ ከስልሳ በላይ ከሆኑት ተከሳሾች ውስጥ አራት ተከሳሾች እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም፡፡ ከነዚህም ውስጥ የጌታስ ኢንተርናሽናል መስራችና ዋና የአክሲዮን ባለድርሻ አቶ ጌቱ ገለቴ ይገኙበታል፡፡ አቶ ገዳ በስር፣ ታደሰ ፈይሳና ነጋ ቴኒ ሌሎች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተከሳች ናቸው፡፡