መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው—አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 2/2008 (ዋኢማ)-በሃገሪቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ፈጣን መረጃ ለተጠቃሚው በመስጠት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው  የመንግስት  ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ።

ለሶስት ቀናት በሃዋሳ ከተማ  ሲካሄድ የቆየው የክልል ኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ተቋማት አመታዊ የጋራ ፎረም ትናንት ተጠናቋል፡፡

ሚኒስትሩ በፎረሙ ማጠቃላያ ላይ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን በፀረ ድህነት ትግሉ የተገኙ ስኬቶችን ብቻ ሳይሆን ድክመቶችን በመጠቆም እንዲስተካከልና የተሻለ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ወቅታዊና ፈጣን  መረጃ ለህዝብ ማድረስ ይገባቸዋል፡፡

ህዝቡ የሚያነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመንግስት በማቅረብና  የሚሰጠውን ምላሽ መረጃን ፈጥኖ በማድረስ ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት   አለባቸው፡፡

መገናኛ ብዙሃን ያላቸው ተደራሽነት ከፍተኛ በመሆኑ ስኬትን መሰረት ባደረገና የህዝብን ጥያቄ መመለስ ባስቻለ መልኩ  ማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀም ጭምር ጠንካራ መልዕክቶች እንዲተላለፉ  ማድረግ እንዳለባቸው  አሳስበዋል።

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ስራዎችን በመፈተሽና ድክመቶችን በማረም የፌዴራል ስርዓቱን ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

" ማንነትን ያከበረች ኢትዮጵያን  ለመመስረትና አንድ ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት ሚዲያው ወጥ  የሆነ መልዕክት በመቅረጽ  በጋራ ማስተላለፍ አለበት" ሲሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በፎረሙ ላይ ከሁሉም ክልሎች እና በፌዴራል ደረጃ ካሉ የኮሙዩኒኬሽንና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት  የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል-ኢዜአ ፡፡