የአገራችን ቱሪዝም ታላላቅ ዕድገት ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1/2008 (ዋኢማ)– ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አገራችን በዓለም ታላላቅ የቱሪዝም ዕድገት ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ራዕይ ማንገቡን አስታወቀ ፡፡

የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሃ ግብር ያሰጠናቸውን 34 ጨምሮ በ1ሺ 239 ተማሪዎች በተለያዩ ደረጃዎች ትናንት አስመርቋል ፡፡

ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ተግኝተው እንዳመለከቱት ፤ኢትዮጵያ በ2012 በቱሪስት መዳረሻነት ከመጀመሪያዎቹ አምስት አፍሪካ አገሮች አንዷ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዓለም ታላላቅ የቱሪዝም ዕድገት ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ራዕይ አንግበው በመስራት ላይ ናቸው ፡፡

አገራችን በ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ሆና በአውሮፓ የቱሪዝም እና የንግድ ካውንስል መመረጧን ጠቅሰው ፤ጠንክሮ ከተሰራ ራዕዩ እንደሚሳካ ማረጋገጫ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ዕድገት እጅግ እምርታ እያሳየ የመጣ ቢሆንም ካለው ፍላጎትና ዕምቅ ሃብት ጋ ሲነጻጸር ገና በርካታ ክፍተቶች የሚታዩበት መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

ስለሆነም በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ማዕከሉ አበረታች ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ምሩቃንም በሙያቸው ቅንና ታማኝ በመሆን ዘርፉን ለማላቅ በሚደረገው ርብርብ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኢንጂነር አይሻ አሳስበዋል ፡፡

የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ በበኩላቸው ተመራቂዎች በዘርፉ በአገራችን ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት የሚመልሱና የህዳሴ ጉዞ በመቀላቀል የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡ ፡

በመጨረሻም በማሰልጠኛ ማዕከሉ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ምርጥ ፈጻሚ መምህራንና ሰራተኞች የተዘጋጀላቸውን ሚዳሊያና ዋንጫ ማግኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡