ኢትዮጵያና አየርላንድ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ገለጹ

ኢትዮጵያና አየርላንድ የቆየ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ገለጹ።

አየርላንድ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ የጀመረችውን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልፃለች።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኤዲያን ኦሃራን ትናንት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያና አየርላንድ ሁለንተናዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

አየርላንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቷን በተግባር ያስመሰከረች መሆኗንም ገልጸዋል።

ይህን የልማት ትብብር አጠናክራ በመቀጠል በሰው ኃይል ልማት መስክ ድጋፍ እንድታደርግ በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

አምባሳደር ኤዲያን ኦሃራ በበኩላቸው አየርላንድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1984 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ድጋፉዋን ስታደርግ ቆይታለች።

በተለይ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግና ከኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ጋር በሚጣጣሙ ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ አገራት ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጎልበት ጥረት ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

በተለይ ተደራራቢ ታክስን በማስቀረት የአገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳለጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ አየርላንዳውያን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አበባን በማምረትና ምግብን በማቀነባበር ሥራ እየተሳተፉ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት በአየርላንዳውያን ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ይዞታዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።

ድርጊቱ አገራቸው ከምታደርገው ተሳትፎ የማያግዳት በመሆኑም በቅርቡ ተጠግነው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

አየርላንድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1994 ኤምባሲዋን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።(ኢዜአ)