ማዕቀቡ ኤርትራ አሸባሪዎችን መደገፍ መቀጠሏን ያረጋግጣል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መራዘም አገሪቷ አካባቢውን ማተራመስና አሸባሪዎችን መደገፍ መቀጠሏን እንደሚያረጋግጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የጦር መሳሪያ ማእቀብ የቆይታ ጊዜን ያራዘመው አሁንም ከአልቃይዳ ጋር ግኑኝነት ያለው አሸባሪ ቡድን አልሸባብ ለደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን በምግለፅ ነው ያለው ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙልጌታ "የማዕቀቡ መራዘም አገሪቷ አሸባሪዎችን መደገፍና ቀጣናውን ማተራመስ አለማቆሟን ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።

የማዕቀቡ መራዘም ኤርትራ ለአሸባሪዎች የምታደርገውን ድጋፍና የምትከተለውን አካባቢውን የማተራመስ ፖሊሲዋን እንደቀጠለችበት ማረጋገጫ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

"በተግባር እያደረገች ያለው ይህንኑ በመሆኑም የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡን አራዝሞታል" ብለዋል።

ኤርትራ ለአልሸባብና ለሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች የምትሰጠው ድጋፍ፣ ከጅቡቲ ጋር የነበራት ግጭትና የምርኮኞች ጉዳይ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታራምደው የማተራመስ ፖሊሲ ለተጣለባት ማዕቀብ መነሻዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ከበርካታ ዓመታት በፊት የተጣለው ማዕቀብ በተደጋጋሚ መራዘሙ አገሪቱ አሁንም በዚሁ ድርጊቷ ገፍታ መቀጠልዋን ያረጋገጠ እንደሆነ ነው አቶ ተወልደ ያስገነዘቡት።

"የአካባቢው አገራት ለህልውናቸውና ለልማታቸው ሰላም ይፈልጋሉ" ያሉት አቶ ተወልደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሚደግፈው ይህንን እንደሆነ አስረድተዋል።

ሰሞኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤቱ በኤርትራ እና ሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማእቀብ ማራዘሙ የሚታወቅ ነው ፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ታህሳስ ወር 2009 ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ጠንቅ የሆነውን አልሸባብን በገንዘብ እና በቁሳቁስ እንደምትደግፍ በማስረጃ በማረጋገጡ በአገሪቱ ላይ የጦር መሳሪያ ግዢ፣ በተመረጡ የመንግስት ባለሰልጣናት ላይ የጉዞ ገደብ እና ሀብታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ማእቀብ መጣሉ ይታወቃል።

እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2009 ላይ አገሪቱ ከጎረቤቷ ጅቡቲ ጋር ጦርነት በመግባት በሃይል ከያዘችው ግዛት ለቃ ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆኗም ማእቀቡ እንዲጣልባት መደረጉንም እንዲሁ -(አዜአ)፡፡