አምስት የኦነግ አባላት ክስ ተመሰረተባቸው

በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባል በመሆን በሞያሌ የፌዴራል ፖሊስ ካምፕ ላይ ጥቃት ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1 መሐመድ አሜ፣ 2 ሰንበቴ በዳኔ፣ 3 ለሊሳ ጋዲሳን ጨምሮ አምስት ግለሰቦች ናቸው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ የሽብር ቡድኑ የደቡብ ዞን አመራር በሆነው በጉልቻ ዴንጌ አማካኝነት የሞያሌ የፌዴራል ፖሊስ ካምፕ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለዋል።

ተከሳሾቹ ተልዕኮ በመቀበል ለጊዜው ካልተያዙ የቡድኑ አባላት ጋር ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በሐምሌ 20 ቀን 2008 . ለሊቱ 9 ሰዓት ላይ ሁለት ክላሽንኮቭ መሳሪያ፣ አራት የክላሽ ካርታ፣ 60 የክላሽንኮቭ ጥይቶች፣ 160 የብሬን ጥይቶች እንዲሁም ሶስት የወገብ ትጥቅ በመያዝ በካምፑ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ነው የተባለው ።

በተኩሱም በሁለት ሚሊሻዎች ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰው ለማመለጥ ሲሞክሩ ከነሙሉ ትጥቃቸው መማረካቸውን በክሱ ተመልክቷል ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው በፈጸሙት የሽብርተኝነት ድርጊት ክስ መስርቶባቸዋል።

ማረሚያ ቤት ተከሳሾቹን ለችሎቱ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ክሱን አሰምቶ ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጥ ይሆናል-(ኤፍ )