የተመድ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ

 

የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን ከአገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ።

ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ኮሚሽነሩ ከ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተወያዩት በሠብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት ጉዳዮች ጉድለቶች መኖራቸውን ገልጸውላቸዋል።

የአገሪቷ ህገ-መንግስት ለሠብዓዊ መብት ትልቅ ሥፍራ መስጠቱን ጠቅሰው አተገባበር ላይ የሚታዩ ጉድለቶች የሠብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያን ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን አቅምና ገለልተኝነት ለማጎልበት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት ችግሮችን በመቀራረብ ለመፍታት ፍቃደኛ ሆኖ የድርድር ሂደት መጀመሩን በጎ ጅምር ሲሉ ገልፀውታል።

ህገ-መንግስቱ ለዜጎች የሰጠው ሙሉ የሠብዓዊ መብት ዋስትና በገዥው ፓርቲ የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም የአገሪቷ ዴሞክራሲ ታዳጊ በመሆኑ የአፈፃፀም ክፍቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

ችግሮችን ለመፍታት ከችግሩ እየተማረና በሂደት እያስተካከለ የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ለኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነር ዘይድ ራድ በበኩላቸው የሚስተዋሉት ችግሮች የሚፈቱት በኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልፀው ከፓርቲዎቹ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየታቸውን አስመልክተው በጉብኝታቸው ማጠቃለያ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በውይይቱ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ቅንጅት፣ መኢአድ፣ አትፓ፣ ኢዴህ፣ ኢፍዴኃግ፣ መኦህዴፓ፣ ኢራፓ እና ገዥው ፓርቲ ተሳትፈዋል-(ኢዜአ) ።