አዲሱ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን የሙከራ ትግበራ በክልሉ 24 መሥ/ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ነው

በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት አዲሱ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን የሙከራ ትግበራ በክልሉ 24 መስሪያ ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለፀ፡፡ የክልሉ አመራር አካላትም በዚሁ ላይ በሃዋሳ ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለስ ዓለሙ በውይይቱ መድረኩ ላይ እንደገለፁት አዲሱ የስራ ምዘና በሲቪል ሰርቪሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና የተረጋጋ እንዲሁም ለውጤት የሚተጋ ሰራተኛ ያለበት ተቋም ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ የሚለውን መርህ ለማስጠበቅና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ የሰራተኛ ፍልሰትን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ 
 ምዘናው የሰራተኛውን የስራ ተነሳሽነት ከመጨመሩም ባለፈ መብቱ የሚከበርበት በመሆኑ የፐብሊክ ሰርቪሱን የአሰራር ስርዓት፣ ስልት እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ወጥና ግልፅ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ዘዴ ነው፡፡ 
 አዲሱ የስራ ምዘና ድልድል በሚካሄድበት ወቅት ሰራተኛውን በግልጽነት፣ በፍትሃዊነትና በተጠያቂነት አወዳድሮ መመደብ እንደሚገባ የገለፁት አቶ መለሰ ዓለሙ በተመዘኑበትና ደረጃ በወጣላቻው የስራ መደቦች ላይ ተገቢውን ሰራተኛ በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ እንደሚገባም አስረድተዋል ፡፡
የሙከራ ትግበራው የድልድል ሥራ በ24 የክልሉ ተቋማት ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ያሉት ኃላፊው በቀሪዎቹ 20 የክልል ተቋማት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በተያዘው ወር መጠናቀቅ እንዳለበት እና ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ካለ በሰኔ ወር የሚፈታበት ጊዜ መሆን እንደሚገባው አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል ፡፡
የሙከራ ትግበራው በተለይ አመራሩ በባለቤትነትና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ትኩረት ሰጥቶ መተግበር እንዳለበት ገልፀው ትግበራውም በተያዘለት መርሃ ግብር መከናወን እንደሚገባውም አቶ መለሰ አሳስበዋል ፡፡
በሹመት ተመድበው በማገልገል ላይ የሚገኙ የስራ ሂደት ባለቤቶች በአዲሱ ጥናት መሰረት የስራ መደቡ የሚጠይቀውን የት/ት ደረጃ፣ የሙያ መስመርና አገልግሎት የሚያሟሉ ከሆነ በቀጥታ የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው መቀጠል እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡