ታንዛንያ ወደቧን በ154 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማስፋፋት ከቻይና ጋር ተስማማች

ታንዛኒያ የሀገሪቱን ዋና ወደብ ለማስፋፋት የ154 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኮንታራት ከቻይና ኩባንያ ጋር መስማማቷን አስታወቀች ።     

ስምምነቱ የወደቡን አቅም በማሳደግ ሀገሪቱንና የወደቡ ተጠቃሚ ሃገራትን የወጭና ገቢ ንግድ ለማጠናከር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ 

የታንዛንያ ዳሪሰላም ወደብ በምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ወደቦች አንዱ ነው፡፡

ይህን ወደብ የሀገሪቱ መንግስት ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ ግብ እንዲመታ የብድር አቅርቦት ለማግኘት የዓለም ባንክን ብድር ቀደም ሲል  ተጠይቆ ነበር ፡፡

እናም የዓለም ባንክ ለወደቡ ማስፋፊያ የ305 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር  የብድር አቅርቦት ባለፈው ጥር ወር ለታንዛኒያ መንግስት ፈቅዷል፡፡

የአሁኑ የ154 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ደግሞ ከዓለም ባንክ ድጋፍ ውጭ ከቻይናው ሃርበር ኢንጅነሪንግ  /ሲ.ኤች.ኢ.ሲ / ጋር የተደረገ የገንዘብ ድጋፍ  ነው፡፡

ግንባታውንም የቻይናው ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ኩባንያ የሚያከናውነው ይሆናል፡፡

ይህ ከፍተኛ የንግድ መዳረሻ የሆነውን የዳሬ ሰላም ወደብ ማስፋፊያ መደረጉን ተከትሎ የሀገሪቱን ወጭና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የታንዛኒያ የአሁኑ የወደብ የማስፋፊያ እቅድ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለውን የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል እንድትሆን ለማድረግ ያሰበችውን  ማሳያ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

የታንዛኒያ ወደብ ማስፋፊያ  ሲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ወደቡ እያስተናገደ ያለውን የ20 ሚሊዮን የኮንቴነር ብዛት ወደ 28 ሚሊዮን የማሳደግ አቅም ይኖረዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና  ግዙፍ ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ ሃገራት ተርታ የምትጠቀሰው ታንዛኒያ ያላትን የወደብ ሃብት፣የባቡር ትራንስፖርት አቅሟን በማጠናከርና የየብስ መንገዶችን በማጎልበት ወደብ አልባ የሆኑ የቀጠናው ሃገራት እያሳዩት ያለውን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለመጠቀም አልማለች፡፡

ለዚህ ማሳያ ደግሞ በታንዛኒያ፣በኬንና ኡጋንዳ የተገኘውን  ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት በርካታ በነዳጅ ማውጣት ዘርፍ ያሉ ኮባንያዎች ልባቸው ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ቀልባቸው እንዲሸፍት እያደረገ ነው፡፡

እናም ይህን ሃብት ለማጓጓዝ የሚያስችል የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ባለመደረጉ ሀገራቱ ካላቸው ሃብት መጠቀም ያልቻሉ በመሆናቸው ታንዛንያም በቀጣይ ክፍተቱን ለመሙላት  እንደምትሰራ አስታውቃለች፡፡    

አሁን ከዓለም ባንክ እና ከቻይናው ሃርበር ኢንጅነሪንግ በተገኘ ብድር እንዲሁም በሃገሪቱ መንግስት የዳሬሰላም ወደብ ማስፋፊያ የሚደረግለት ይሆናል፡፡ 

በምስራቅ አፍሪካ የዚህ ወደብ ተቀናቃኝ የሆነው የኬንያው የሞምባሳ ወደብ ፤ ወደብ አልባ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት እያገለገለ ይገኛል፡፡

እኤአ በ2014 የዓለምባንክ ባወጣው ሪፓርት እንዳመላከተው የገቢ እቃዎችን ለማስተናገድ የዳሪሰላም ወደብ አቅሙ አናሳ በመሆኑ ምክንያት ታንዛኒያንና ተጎራባች ሃገራትን በዓመት እስከ 2.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው ነው፡( ምንጭ:   ሮይተርስ )