የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 35 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች መሳሪያ በመታጠቅና ጫካ በመግባት አመጽ በማስነሳት በንጹሃን ዜጎች እና በመንግስት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ 35 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ ዛሬ ከሰዓት  በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው የቀረበው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ተሻገር ወልደ ሚካኤል፣ 2ኛ ነጋ ዘላለም፤ 3ኛ ተስፋሁን ማንደፍሮን ጨምሮ 35 የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሽብር ድርጅት አባላት ናቸው።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመላከተው ተከሳሾቹ ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ባሉት ጊዜያት መሳሪያ በመታጠቀ አሜሪካ፣ ጀርመን ስዊድን እና ኤርትራ ከሚኖሩ ከሽብር ቡድኑ አመራሮቸ 800 ሺህ ብር በመቀበል አባላትን በመመልመል እና በማደራጀት ጫካ በመግባት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር አካባቢ አመጽ ማስነሳታቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በአካባቢው በንጹሃን ዜጎች፣ በመንግስት ተቋማትና በጸጥታ ሃይሎች ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውም በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ማንነታቸው የተለየና የክሱ ሰነድ የደረሳቸው ሲሆን፥ ከጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡና ክሱን በችሎት ለማሰማት ለሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል(ኤፍ ቢ ሲ) ።