እስራኤል በምዕራብ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል የሚውል የ 1 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረች

እስራኤል በምዕራብ አፍሪካ ባሉ 15 ሃገራት ላይ ለታዳሽ ኃይል ማስፋፊያ የሚውል የ1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገች፡፡

እስራኤል በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክት የሚውል የ1 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ ነዋይ ልታፈስ  ነው፡፡  

የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ወደፊት የአረንጓዴ ኃይል ፕሮጀክቶችን የሚያጎለብት ነው ተብሏል ፡፡

መሠረቱን እየሩሳሌም ያደረገው ኢነርጂያ ግሎባል የተሰኘው የታዳሽ ኃይል ኩባንያ ፕሮጀክቱን በ15 የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ላይ ለመተግበር ያቀደ ሲሆን ስምምነቱ በእስራኤልና የምዕራብ አፍሪካ  ሃገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር ነው የተፈፀመው፡፡

የኢነርጂያ ግሎባል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሴፍ አብራሞዊትዝ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ይህን በፀሃይ ሃይል የሚሠራ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት በሁሉም የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል ሃገራት በመገንባት የፋይናንስ፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲስፋፋ ለማድረግ እንዲሁም የእውቀት ሽግግርን ለማራመድ ያለመ ፕሮጀክት ነው፡፡

ኢነርጂያ ግሎባልና ሌሎች አጋር ኩባንያዎች የመጀመሪያውን የታዳሽ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክት በሩዋንዳ  በማካሄድ በሃገሪቱ የኃይል ምንጭ 6 ከመቶ አንዲያድግ አስተዋጽኦ ማበርከቱ  ነው የተገለጸው ፡፡ በተመሳሳይም በቡሩንዲም 15 ከመቶ በመጨመር ውጤት ማሳየቱ ተነግሯል፡፡

ከ600 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፈጽሞ የማያገኙ በመሆኑ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማሟላት በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል ሃገራት ላይ ለአራት አመታት የሚቆይ  የአንድ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ እንደተደረገ ተመልክቷል፡፡

በፕሮጀክቱ ውስጥ ከተካተቱ ሃገራት መካከል ላይቤሪያ ትገኝበታለች፡፡ ይህ ደግሞ በሁለቱ ሃገራት ያለው ግንኙነት የሚያዳብር እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡

በኢነርጂያ ግሎባል እና በአለም አቀፍ አጋሮች በሚደረገው የፋይናንስ ድጋፍ አማካኝነት በሚካሄደው ፕሮጀክት በዚህ ዓመት መጀመሪያው ኢንቨስትመንት 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የታዳሽ ሃይል ፕሮጀክቱ ላይበሪያ ላይ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የእስራኤልና የአፍሪካ መሪዎች በመጪው ጥቅምት ቶጎ በሚያደርጉት  የጋራ ስብሰባ ላይ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ 10 የአፍሪካ ሃገራት ላይ ፕሮጀክቱን ይፋ እንደሚደረግ የዘገበው ዘ ታወር የተሰኘው ድረ ገፅ ነው፡፡