ቦርዱ በሁከት ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የገቡ ዜጎች ሰብዓዊ አያያዝ መልካም መሆኑን አስታወቀ

በሁከትና ብጥብጥ ወንጀል በመሳተፍ ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ እንዳስታወቁት መርማሪ ቦርዱ የተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ

መብት አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ በሶስት ዙር ግምገማ አካሂዷል።

በዚህ መሰረትም ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ በማቆያ ቤት በሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ችግሮች ማግኘቱንና ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን መከናወናቸውን ነው ያስታወቁት።

መርማሪ ቦርዱ በህገ-መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የእስረኞችን የሰብዓዊ መብት አያያዝና ሌሎች ጉዳዮችን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመመርመር ስራዎችን ይሰራል።

በተለይም በመጀመሪያው ስድስት ወር አካባቢ ከእስረኞች ቁጥር መብዛት ጋር የተያያዙ የምግብ እጥረት፣ የመኝታ መጣበብ፣ የህክምና እጥረትና ሌሎች ችግሮችን ተመልክቶ እንዲፈቱ አድርጓል ብለዋል አቶ ታደሰ።

አንደኛ አስገድደው ቃል እንዲሰጡ የማድረግ ሁኔታ በተወሰኑ የማቆያ ቦታዎች በተወሰኑ የፀጥታ ሃይሎች እንደተፈፀሙ አይተናልብለዋል ።

 በሌላ በኩል ከምግብ እጥረት፣ ከመኝታ ጥበት፣ ከውሃ አቅርቦት ችግር በሌላ በኩል ደግሞ ከጤና አገልግሎት ከመፀዳጃ ቤት ችግር ከአልባሳት ጋር የተያያዙ እነዚህ ችግሮች በስፋት ነበሩ እና በወቅቱ ግን በአስቸኳይ እንዲፈቱ የተደረጉ ናቸው በማለት አብራርተዋል ።  

እነዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ጊዜ ላይ መርማሪ ቦርዱ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን የገለፁት ሰብሳቢው መንግስት ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች በተለያዩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የተሳሳተ መረጃ መሳተፋቸውን አውቆ በማስተማር ከእስር መልቀቁ እንደ ጠንካራ ጎን መገምገሙን ገልፀዋል።

መርማሪ ቦርዱ ያያቸውን ሁኔታዎች ለመንግስት ባቀረበው መሰረትም ከላይ የታዩ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ክፍተቶችን  ፈጥኖ ከማስተካከልና ጥፋቱን የፈፀሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድም ጥሩ ስራ ሰርቷል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተዘዋወረበት ወቅት ከተለያዩ የማህበረሰቡ አካላት ጋር የተገናኘ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ዘላቂነት ያለው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

ሰላሙ ቀጥሏል ህብረተሰቡን ከዕለታዊ ስራው የሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች የሉም በሌላ በኩል ደግሞ አመራሩ ሙሉ በሙሉ የፀጥታ አመራሩም ይሁን የአስተዳደር መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ እየሰራ ነው ብለዋል ።  

በአገሪቱም በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ ቀጣይነት ያለው ሰላም ሰፍኗል ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ነው ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑንና በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆኑን በአዋጁ የስድስት ወር ቆይታ መታየቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥልቅ ተሃድሶው የተቀየሩ አዳዲስ አመራሮች ከህብረተሰቡ ጋር መስራት መጀመራቸውንና ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ መሆኑንም ሰብሳቢው ተናግረዋል።( ምንጭ: ኢዜአ)