በጋምቤላ ተገቢ ያልሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃድና ካርታ የሰጡ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች ተቀጡ

በጋምቤላ ክልል ከ28 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች ተገቢ ያልሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃድና የመሬት ካርታ የሰጡ 10 የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እና የመሬት አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ከ3 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ፡፡

የክልሉ የስነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ የመንግስትን ስራ በማያመች ሁኔታ በመምራት ወንጀሉን የፈፀሙት ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ነው፡፡

የክልሉ የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን የካርታ ስራ ባለሙያ እና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሃይለማርያም በሃይሉ ለ13 ባለሃብቶች ተገቢ ያልሆነ የመሬት ካርታ መስጠታቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

የባለስልጣኑ የዳታ ሲስተም ባለሙያ አቶ አበራ ምርከና ለአራት ባለሃብቶች ተደራራቢ ካርታ መስጠታቸውንም ዓቃቢ ህግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

የባለስልጣኑ መሬት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሃላፊ ተወካይ አቶ መብራቴ ለማን ጨምሮ አራት ባለሙያዎች 18 የመሬት ካርታ በህገወጥ መልኩ መስጠታቸውም በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

በክሱ ላይ እንደተጠቀሰው የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ሚጎ፤ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከአሰራር ውጭ ለ28 ባለሃብቶች ሰጥተዋል በሚል ተከሰዋል፡፡ 

የኤጀንሲው የቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ኪያድ ኪያንግ እና የፍቃድ ዘርፍ የስራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ ሳምሶን ዳክን ጨምሮ አምስት ሰራተኞች በድርጊቱ መሳተፋቸውንም ዓቃቢ ህጉ በክሱ አቅርቧል፡፡

የአበቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡሶ ኡጫን ያለአግባብ መሬት መስጠታቸውም በዓቃቢ ህግ ክስ ተመላክቷል፡፡

ግለሰቦቹ እያንዳንዳቸው ከሁለት በላይ ህገወጥ ፍቃድ መስጠታቸውና ከጋምቤላ ክልል ውጭ በደቡብ ክልል የተካለለ ተጨማሪ ካሬ ሜትር ይዞታን መስጠታቸውም በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱን ክደው ቢከራከሩም ዓቃቢ ህግ ያቀረበውን የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተንነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት የጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው የወንጀል ችሎት አቶ ቦለ ሬክ የተባሉ ተከሳሽ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ብይን ሰጥቷል፡፡

የአበቦ ወረዳ አስተዳዳሪን በሶስት ዓመት ፅኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡና በባንካ ሂሳባቸው የሚገኝ 347 ሺህ 531 ብር እንዲወረስም አዟል፡፡

አቶ ኡጁሉ ሚጎ በ3 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ብይን የሰጠው ፍርድ ቤቱ በባንክ ሂሳባቸው የሚገኝ 89 ሺህ ብር እንዲወረስም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀሪዎቹ ተከሳሾች በ3 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በሌላ በኩል ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማፍራት ወንጀል የተከሰሱት አቶ መንድሙ ተካ እና አቶ ቱት ኮር ጉዳያቸው ተጣርቶ በነጻ ተለቀዋል-(ኤፍ. ቢ. ሲ) ፡፡