የፕሬዚደንት ትራምፕ ልጅ በአባቱ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሩሲያ መረጃ ተቀብሏል ተባለ

የፕሬዚደንት ትራምፕ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር አባቱ በ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ከሩሲያ ሰዎች ጋር በመገናኘት መረጃ መቀበላቸው እየተነገረ  ይገኛል ።                 

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር አባቱ በ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከሩሲያ ጋር በድብቅ ተመሳጥረው የምርጫውን ውጤት አስቀይረዋል ተብለው በተጠረጠሩበት ጉዳይ ከሩሲያ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ መረጃ ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል ፡፡

ትራምፕ ጁኒየር በሠጠው ምላሽ በስብሰባው ላይ ተገኝቻለሁ ነገርግን ሂላሪ ክሊንተንን የሚጎዳ መረጃ አልተቀበልኩም ብሏል፡፡  

የሜይን ግዛት እንደራሴ የሆኑት እና ከራሳቸው ከዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ የተገኙት ሴናተር ሱዛን ኮሊንስ በትራምፕና በሩሲያ መካከል ስለሚነሳው ግንኙነነት መጣራት ካለባቸው ጉዳዮች አንዱ የፕሬዝዳንቱ ወንድ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር ከሩሲያ መሪዎች ጋር ያለው ግንኙነት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የሴኔቱ የምርመራ ኮሚቴ ጁኒየርን አቅርቦት በተለይም በምርጫው ዋዜማ ላይ በክሬሚሊን ጉዳይ ከሩሲያዊው የህግ ባለሙያ ጋር ያካሄደውን ውይይት እና ስላለው ግንኙነት ቃለ መጠይቅ ሊያደርግለት ይገባል ብለዋል እንደራሴዋ፡፡

ከስብሰባው በኋላ ትራምፕ ጁኒየር በምርጫ እኤአ በ2016 የአባቱ አደገኛ ተፎካካሪ ስለነበሩት ስለ ሂላሪ ክሊንተን ክብራቸውን የሚነኩ መረጃዎችን ለማሠራጨት መዛቱን ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ጽፏል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር ከሩሲያው የህግ ባለሙያ ጋር ያደረጉትን ስብሰባ በተመለከተ እሱን እና ሌሎች በስብሰባው ላይ የተሳተፉ ሰዎችን ግንኙነት መርማሪ ኮሚቴው ማጣራት አለበት ያሉት ሱዛን እሳቸውም የኮሚቴው አባል እንደመሆናቸው ጉዳዩን በትኩረት ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በስብሰባው ላይ ከጁኒየር በተጨማሪ የቀድሞው የፕሬዝዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊ ፖል ማናፎርት እና የፕሬዝዳንቱ የእንጀራ ልጅ ጃሬድ ኩሽነር ታድመው ነበር፡፡

ጁኒየር በጉዳዩ ላይ እጁ እንደሌለበትና ከሩሲያው የህግ ሰው ስለ ሂላሪ ክሊንተን ምንም አይነት መረጃ አልተቀበኩም ሲል ቢያስተባብልም በስፍራው መገኘቱን ግን አምኗል፡፡

አሁን ደግሞ ሲናተር ሱዛን መጠየቅ አለበት ካሉት በኋላ ጁኒየር የሴናተሯ አነጋገር በግልፅ መረጃ ያልተደገፈ የተምታታ አሻሚና ትርጉም የሌለው ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡

በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ ማጣራት የሚፈልገው ነገር ካለ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑንንም ገልጿል፡፡ አጣሪ ኮሚቴው የሚጠይቀኝን ሁሉ ለመናገር ዝግጁ ነኝ በማለት፡፡ የክሬሚሊን ባለስልጣናትም በበኩላቸው ስለተባለው ነገር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ያም ሆኖ የኮሚቴው አጣሪ ቡድን ዝርዝር ጉዳዮችን እያየ በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ የኦክላሆማው ተወካይ የሪፐብሊካን እንደራሴ ጀምስ ላንክፎርድ ገልፀዋል፡፡

የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) እና የኮንግረሱ መርማሪ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ስላላቸው የሚስጥር ግንኙነት እና ስለ 2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቀደም ብሎ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሶ የዘገበው ፕሬስ ቲቪ ነው፡፡