በሙስና የተጠረጠሩን በቁጥጥር ስራ የማዋል ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል -ኮሚሽነሩ

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌዴራልና የክልሎች የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥምረት 22ኛ መደበኛ የጋራ ጉባኤ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን በጉባኤው መክፈቻ ላይ እደገለጹት፤ የሙስና ወንጀልን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ለመከላከልና ተግባሩንም ከምንጩ ለማድረቅ የሁሉንም አካላት ርብርብና ተሳትፎ ይጠይቃል።

ህብረተሰቡን እያማረሩ የሚገኙ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን አስቀድሞ የመከላከልና የህግ ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በቅርቡም መንግስት ሙሰኞችን ለህግ ለማቅረብ በጀመረው የተጠናከረ እንቅስቃሴ ከ40 በላይ የስራ ኃላፊዎችና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ይሄው ተግባር በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር አሊ ጠቁመው ክልሎችም የትግሉን አቅጣጫ እንዲከተሉ አስገንዝበዋል።

''የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስ የፌዴራልና የክልል የፀረ-ሙስና ተቋማት ህዝቡን የትግሉ አጋር በማድረግ የመሪነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል'' ብለዋል።

ተቋማቱ ከፍተኛ የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በመንግስት ግዥ፤ ሽያጭና በመሬት አስተዳደር ላይ ባከናወኗቸው ስራዎች የመንግስትና የህዝብ ሃብትን መታደግ መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎችም ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ በማረምና በቀጣይ የፀረ-ሙስና ትግል ዕቅዶችን ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጡ ኮሚሽነር አሊ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላችው ሀገሪቱ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን አምርሮ መታገል ያስፈልጋል።

''በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ ሙስናን መከላከል አይቻልም'' ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በየደረጃው ያሉ ተቋማትና ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት የተቀናጀ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዛሬ የተጀመረውና ለሶስት ቀናት በሚቆየው የጥምረቱ የጋራ ጉባኤ ላይ የፌዴራልና የሁሉም ክልሎች የፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና ዳይሬክተሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በቆይታቸውም በ2009 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና እንቅስቃሴና የመልካም አስተዳደር ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ  ታውቋል ኢዜአ ፡፡