ኢራን በአሜሪካ የተጣለባትን አዲስ ማዕቀብ እንዲነሳላት እንደምትጠይቅ አስታወቀች   

ኢራን በአሜሪካ የተጣለባትን አዲስ ማዕቀብ እንዲነሳላት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰሚ አካላትን  እንደምትጠይቅ አስታወቀች፡፡

የአሁኑን የአሜሪካ ውሳኔን መሠረት በማድረግ ሁሉም ኢራናዊ በአንድነት እንዲቆምም የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሀኒ ጠይቀዋል፡፡

የኢራንና የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ የማይዋጥላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ በሶስት ሀገራት ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ አዲስ ማዕቀብ ፈረመዋል፡፡

በተለይም ደግሞ እሳቸው አሁን በትረ ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው አስቀድመው አሜሪካ እኤአ በ2015 የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ኢራን የምታደርገውን የኔውክለር ኃይል ግንባታ ለሰላማዊ ዓላማ እንድታውልና በአንጻሩ ደግሞ አሜሪካ በሀገሪቱ ላይ ጥላው የቆየችው ማዕቀብ እንዲነሳላት ስምምነት ላይ መደረሱ በእጅጉ ሲኮንኑ ቆይተዋል፡፡ ይህ ስምምነት በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አስቀያሚውና ሀገሪቱ ከሰራቻቸው ስህተቶች ውስጥ በግብባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሉም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

ኢራን በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፍ ሀገራትና ከአሜሪካ ጋር እያገገመ የመጣው ግንኙነቷ የትራምፕ የአሁኑ ውሳኔ ሀገሪቱ ዳግም ከዓለም እንድትገለል ያሰበ ድርጊት ነውም ትላለች ሀገሪቷ፡፡

ይህ ውሳኔ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሃኒ ሀገራቸው ከየትኛው የዓለም ሀገር ለመነጠል እንደማትፈልግና ከአሁን ቀደም ደርሶባት የነበረው መገለል በሀገሪቱ ያሳረፈውን ጠባሳ በማስታወስ የአሁኑን የትራምፕ ውሳኔ አውግዘዋል፡፡

በሩሃኒ ዘመን ኢራን ተጥሎባት የቆየው ማዕቀብ የተነሳበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ በእሳቸው ዘመን ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር ሻክሮ የቆየው ግንኙነት የተመለሰበት ቢሆንም አሁንም ግን ሀገሪቱ በአሜሪካ የተላለፈባት ውሳኔ ዳግም የሀገሪቱን ግንኙነት የሚያበላሽ ድርጊት ነው ይላሉ  ሩሃኒ፡፡

ስለሆነም ይላሉ እሳቸው ሀገሬ ከየትኛውም የዓለም ሀገር መነጠልን አትፈልግም የአሁኑን የአሜሪካን ውሳኔም ቢሆን ዳግም ለማግባባት ሁለተኛ የዴፕሎማሲ ጥረቴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡

መነጠልን በየትኛውም መንገድ አንቀበልም ሲሉ በቴህራን ለተሰበሰቡ ፖለቲከኞችና የወታደራዊና ኃይል አመራሮቻቸው ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ በኢራን ላይ አሁን ያሳለፈችው ውሳኔ የተናጠል ውሳኔ ብቻ አይደለም በስሯ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ቻይናና ጀርመንን ያሳተፈ ነው፡፡

ማዕቀቡለኢራን ከባድና መልሳ ያገኘችውን በነጻነት ከእነዚህ ሀገራት የምታደርገውን ግንኙነት የሚያጠለሽ ተግባር ይሆናል፡፡

ተራማጅ አስተሳሰብን የሚያራምዱት የስልሳ ስምንት ዓመቱ ሩሃኒ  ከወግ አጥባቂ የኢራን ፖለቲከኞች አሁን በምዕራባዊያን ሀገራት የደረሰባቸውን ማዕቀብ ለማለሳለስ የሚያደርጉትን ጥረት ቢያጣጥሎባቸውም እሳቸው ግን አሁን መላው ኢራናዊያን አንድነት ያስፈልገናል እያሉ ነው፡፡

እናም በኢራን ጉዳይ ሁሉም ዜጋ ህብረትን በማጠናከር ሀገርን ከሚያፈራርሱ ድርጊቶች በመቆጠብ ሀገረን ለመገንባት ህብረታችን ከየትኛው ጊዜ በላይ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

አሜሪካ ከሰሞኑ በኢራን፣ ሩሲያና ሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ማዕቀብ አሳልፋለች፡፡ ሩሲያ የአሜሪካን ድርጊት የኢኮኖሚ ጦርነት ስትለው ኢራን ደግሞ ለየትኛውም ዓለም አቀፍ ሰሚ አካል አሁን አሜሪካ በሀገሪቱ ላይ ያሳለፈችውን ውሳኔ ለማሰማት እንደተዘጋጀች አስታውቃለች፡፡