በምስራቅ ሀረርጌ ዞን 49 ቀበሌዎች በኦሮሚያ ስር እንዲተዳደሩ መካለላቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን 49 ቀበሌዎች በኦሮሚያ ክልል ስር እንዲካለሉ መደረጉን የክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መሃል ሲስታዋል የነበረውን ችግር ለመፍታት የወሰን ማካለል ስራ እየተሰራ መሆኑንም የቢሮው ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው የወሰን ችግር በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶችን በማስከተል ለበርካታ ሰዎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ነበር።

በ1997 የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ መሰረት በማድረገግ ከወሰን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱም ክልሎች ከስምምነት መድረሳቸውን ያስታወሱት ሃላፊው፤ በስምምነቱ መሰረት ወሰን የማካለሉ ስራን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም መሰረት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች በሁለቱም ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳባቸው ከነበሩ 68 ቀበሌዎች 48ቱ በኦሮሚያ ክልል ስር እንዲተዳደሩ የሚያደርግ የማካለል ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል ።

የ19 ቀበሌዎችን ወሰን የማካለሉ ስራ አሁንም ቀጥሏል ያሉት አቶ አዲሱ፤ ወሰን የማካለል ስራውም በቁንቢ ወረዳ 3 ቀበሌዎች፣ በአመዩ ወረዳ 4 ቀበሌዎች፣ በሚደጋ ቶላ ወረዳ 2 ቀበሌዎች፣ በጉርሱም ወረዳ 2 ቀበሌዎች፣ በጭናክሰን ወረዳ 2 ቀበሌዎች እንዲሁም በሜታ ወረዳ የሚገኝ 1 ቀበሌ ነው ብለዋል።

ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ግጭት በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ላይ በመመርኮዝ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በመፍታት ድንበር አካባቢ ያሉ አስተዳደሮች የግጭት እና የሰዎች ህይወት የሚያልፍባቸው ሳይሆን ሰላምና ልማት የሚረጋገጥበት እንዲሁም የህዝቦች ወንድማማችነት የሚመሰረትበት ስፍራ እንዲሆን የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሰላም እና በብስለት እንዲሁም ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከወሰን ጋር በተያያዘ ከክልሉ አዋሳኝ ከሆኑ ጎረቤት ክልሎች ጋር የሚነሱ ችግሮችን ሰላማዊ እና ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ አዲሱ አረጋ አያይዘው ጠቁመዋል።

በዚህ መልኩም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ ሲስተዋል የነበረ ችግር የወሰን ማካለል ስራ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

ከጋምቤላ፣ ከአማራ እና ከደቡብ ክልሎች ጋር ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችንም የክልሉ መንግስት ሰላማዊ በሆነ እና ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለመፍታት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።