የታላቁ መሪ ራዕይ በትውልድ ቅብብሎሽ ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚንስትር ኃለማርያም

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ራዕይ በትውልድ ቅብብሎሽ ቀጣይ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የታላቁ መሪ 5 ዓመት መታሰቢያ ላይ ገለጹ፡፡

በመለስ ዜናዊ የሕዝብ መናፈሻና ቤተመጽሐፍት (ፓርክ) ዛሬ መታሰቢያው ሲከበር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳስገነዘቡት ፤ታላቁ መሪ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ፍትሐዊ የዓለም ሥርዓትን ግንባታ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ይቀጥላል፡፡

በመለስ አስተምህሮት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በመታገዝ የመለስን ራዕይ እውን ለማድረግ አመራሩ ዝግጁ እንደሆነ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁሲሉ አቶ ኃይለማርያም ገልጸዋል፡፡

2ኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠቅላይ ሚንስትሩ አሳስበዋል፡፡

የመለስ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ የመለስ አስተምህሮትን በተደራጀ መልኩ ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ቁጥራቸው 400 አካባቢ የሚደረሱ የታላቁ መሪ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን እንዳሰባሰበና በመጪው ሮብ አንድ መጽሐፍ እንደሚያስመርቅ ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ የእንግዶች ማረፊያ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ ቤተመፅሐፍት፣ ፋውንዴሽኑ ቢሮ፣ ሰገነት እና የታላቁ መሪ አፅም ማረፊያ ሕንፃዎች እየተገነቡለት እንደሆነና ግንባታውን በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ወይዘሮ አዜብ አክለው ገልጸዋል፡፡

ታላቁን መሪ ማጣት ሐዘኑ መራር ቢሆንም ሕያው በሆኑ የመለስ አስተምህሮቶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመታገዝ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ባለችው የዕድገት ግስጋሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የትግል አጋሮች እንዲሁም ቤተሰቡ ይጽናናሉ፡፡ብለዋል ወይዘሮ አዜብ፡፡

በዕለቱ በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የችግኝ ተከላ፣ በመለስ ዜናዊ የሕዝብ መናፈሻና ቤተ መጽሐፍት በብሄር ብሄረሰቦች የተሰየሙ መንገዶች ላይ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ እና  ጉብኝት በፓርኩ ተከናውነዋል፡፡

የታላቁ መሪ 5 ዓመት መታሰቢያየሐሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪበሚል መሪቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ መሆኑን ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡