የአፋር ብሔራዊ ክልል ከሦስት ወራት በኋላ ለሚያስተናግደው 12ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በድምቀት ለማክበር የተለያዩ አስፈላጊ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን አስታወቀ ።
በክልሉ የ12ኛው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አስተባባሪ ኮሚቴ ኃላፊ ሞሃመድ አወል አብዱርሃማን ለዋሚኮ እንደገለጹት ከሦስት ወራት በኋላ የሰመራ ከተማ የምታስተናግደውን የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ደማቅ ለማድረግ አምስት የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ይገኛል ።
የክልሉ መንግሥት በዓሉን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል አቶ ሞሃመድ ። የአፋር ክልል ከብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በተየያዘ የሁለት መንገዶች፣ የስታዲየም፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን አቶ ሞሃመድ ተናግረዋል ።
የፌደራል መንግሥት የሰመራን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ፕሮጀክትን ከብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በፊት አንዲጠናቀቅ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ ሞሃመድ አመልክተዋል ።
በአሁኑ ወቅት እንግዶችን ያስተናግዳሉ ተብለው የሚጠበቁት የሆቴሎች ግንባታ ሥራ እንደ ዕቅዱም ባይሆን በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አቶ ሞሃመድ ተናግረዋል ።
12ኛውን የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን በደማቅ ሥነ ሥርዓት ለማክበር የፌደራል መንግሥት ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቀናጅተው በዓሉን ለማድመቅ እየተጉ ይገኛል ።
11ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሓረር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል ።