አዲሱን ዓመት ለመቀበል የአስር ቀናት ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

በሀገር አቀፍ ደረጃ የ2010ዓ.ም. አዲስ ዓመት ለመቀበል  አስር ሁነቶች መዘጋጀታቸው የፌደራል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜ 5፣ 2009ዓ.ም. ድረስ ባሉት አስር ቀናት የሚከናወኑት ሁነቶች ባለፉት ዓመታት በመንግስትና ሕዝብ ጥረትና ርብርብ ሀገሪቷ በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን የልማት ውጤቶች ይበልጥ በማጠናከርና በ2017ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ያስቀመጠቸውን ግብ እውን ለማድረግ ያግዛሉ ፡፡

ከአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል በኋላ በተቆጠሩት አስር አመታት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋትና ድክመቶችን በማረም፣ ብሔራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ ሁነቶቹ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል ፡፡

በዚህም መሰረት   ነሐሴ 26 የፍቅር ቀን፣

ነሐሴ 27 የእናቶችና የሕጻናት ቀን፣

ነሐሴ 28 የአረጋውያን ቀን፣

ነሐሴ 29 የሰላም ቀን፣

ነሐሴ 30 የንባብ ቀን፣

ጳጉሜ 1 የአረንጓዴ ልማት ቀን፣

ጳጉሜ 2 የመከባበር ቀን፣

ጳጉሜ 3 ሀገር ፍቅር ቀን፣

የጳጉሜ 4 የአንድነት ቀን እንዲሁም

ጳጉሜ 5 የኢትዮጵያ ቀን በሚል ተሰይመዋል፡፡

እነዚህን ቀናት በዘላቂነት ለማክበርና የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ሕዝቡ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የሚዲያ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ዶክተር ነገሬ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡