የኢትዮጵያን ህዳሴ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ዜጋ በአንድነት መስራት ይኖርበታል-ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ

የኢትዮጵያን ህዳሴ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ዜጋ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

“መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚተገበር ሀገራዊ ኩነት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

የመርሃ ግብሩን መጀመር ይፋ ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ፥ ባለፉት 10 ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ችግሮችን ለማስወገድ ህዝቡ በአንድ ስሜት መነሳት ይኖርበታል ብለዋል።

ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በጋራ ለመስራት ቃል በገቡት መሰረት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ይህም ሀገሪቱ በዓለም ቀዳሚ የሆነ ፈጣን እድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰው፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ሀገራት ሰላም የምትተጋ ሀገር ሆናለች ነው ያሉት።

ህዝቦች እኩልና ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፋ በራሷ አቅም እየሰራች እንደምትገኝ ማስመስከሯን ጠቅሰዋል።

ሆኖም የልማትና የፀረ ድህነት ትግሉ ስኬታማ እንዳይሆን የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ቁጥር በየጊዜው መጨመሩን ተከትሎ በስራ እድል ፈጠራው ላይ በስፋት ባለመሰራቱ የመጣው ስራ አጥነት ፈታኝ እንደነበሩ ነው ያስገነዘቡት ።

ባለፉት 10 ዓመታት የስነምግባርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ለእድገቱና ለትግሉ ማነቆ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት ።

ፕሬዚዳንቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀርፎ ወደ እድገት ለሚደረገው ጉዞ ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲረባረብና ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ይፋ የሆነው መርሃ ግብርም ህብረተሰቡ ከ10 ዓመት በፊት የገባውን ቀል ኪዳን ዳግም የሚያድስበትና መነሳሳትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ አስታውቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን ድረስ ያሉት ተከታታይ 10 ቀናትም የተለያዩ ስማያሜና መርሃ ግብር ተዘጋጅቶላቸው መንግስትና ህዝብ በርካታ ስራዎችን አብርው በመስራት አዲሱን ዓመት በተለየ መልኩ ለመቀበል ዝግጅት እነደተደረገ መገለጹ የሚታወቅ ነው ።

ፕሬዚዳንቱ በዝግጅቶቹ ላይ የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዓሉ ለየት ባለሁኔታ ሲከበር በአጠቃላይ የዜጎች ጥቅም ላይ ትኩረት አድርጎ አዲሱን ዓመት ለመቀበል መሆኑን በመግለጽ-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።