መልካም አስተዳደርን ለመገንባት ይዋል ይደር አይባልም

በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዘረጋ ሁለት አሥርት ዓመታት አልፈዋል። በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀምም ቁጥራችው ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሥርተው አጀንዳቸውን ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ባለፉት ሃያ ዓመታት በየአምስት ዓመቱ በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ላይ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው ተሳትፎም ሲታይ የጎላ እንደነበር የሚታወስ ነው።

 

ይሁንና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የህዝቡን ይሁንታና ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ እንዳሉ ቢታወቅም በተቃራኒው አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ስም ሕገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ይታያሉ። የዜጎችን መብትና እኩልነት ያረጋገጠውና ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት ያለምንም ተጽዕኖ ተደራጅተው እንዲሳተፉ ሙሉ ነጻነታቸውን ያጎናፀፈ የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመናድ ያለመ  እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።

 

ህልውናው የፈጠረላቸውንና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻላቸውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረው መንቀሳቀስና የፖለቲካ አጀንዳቸውን ወደ ሕዝብ ዘንድ በማስረፅ በምርጫ አሸንፈው ወደ ኃላፊነት መምጣት የሚያስችላቸውን ቀና መንገድ ከመከተል ይልቅ ይህ ነው የሚባል አጀንዳ ሳይዙ በሕዝቡ መካከል ሁከትና ትርምስን በመፍጠር በግርግር ለመጠቀም አልመው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕገ መንግሥቱን ሲተላለፉ ይስተዋላሉ።

 

በቀደሙት ዓመታት በአገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያራምዷቸው ሕጋዊነት የጎደላቸው ተግባራት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ጥያቄ ያስነሱ እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይም አገራችን የምታካሂዳቸውን ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጣጣልና ተገቢ ያልሆነና የተዛቡ አስተያየቶችን በመስጠት የአገሪቱን ብሄራዊ  ደህንነት ሊፈታተኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ውሣኔዎችን በመቃወምና ከአገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበርና በመተጋገዝ የተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ መስተዋላቸው ይታወቃል። ይህም ሆኖ ግን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት በመናድ የልማታዊ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

 

በገጠር የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት ለመናድ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል። በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ሰው በላውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በከተማም ሆነ በገጠር ኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የተንሰራፋበትና ልማታዊ አስተሳሰብ የሚባል ነገር ያልነበረበት ሁኔታ ነበር።

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገጠር የመሬት ክፍፍል የተደረገ እና አርሶ አደሩ መሬት ያገኘበት ሁኔታ ቢኖርም አንዳንድ የፍትሃዊነት ችግሮችን የማስተካከል ሥራ በመከወንና በአንዳንድ አካባቢ የነበሩ በተገቢው መልክ ክፍፍሉ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች ብቻ የማስተካከያ ተግባሮችን በመፈፀም ባለበት እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ በአርሶ አደሩ ዘንድ የነበረ ኋላ ቀር አስተሳሰብን ለመቅረፍ ያላሳለሰ ጥረት ተደርጓል።

 

አርሶ አደሩ በላቡ ሰርቶ ጥሮና ግሮ አኗኗሩን መቀየር የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸትና የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተሰራው ሥራ በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ዋስትና ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻውን መወጣት እየቻለ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለመዝጋት የተደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደነበረው ለማየት ይቻላል።

 

አርሶ አደሩ በተሰጠው የእርሻ ቦታ ላይ የራሱንና የቤተሰቡን ላብ አፍስሶና በመንግሥት ከሚመደቡ ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እያገኘ ሰርቶ ከድህነት መላቀቅ የሚቻል መሆኑን በተግባር በመገንዘቡ ልማታዊነቱ ባደገ ቁጥር በገጠር የኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት እየተናደ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

በአሁኑ ወቅት ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስተርነት የተቀየሩ አርሶ አደሮች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በገጠር ሞዴል አርሶ አደሮች ሌላውን እየመሩና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመሰባሰብ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተው ልማታቸውን እያረጋገጡ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

 

ይህ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት መናድ ሌላው ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መልክ ልማታዊነት እየተረጋገጠና ኪራይ ሰብሳቢነትን ነቅሎ ለመጣል እየተናነቀ ይገኛል። በከተማም በተመሳሳይ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢነትን የበላይነት ለመድፈቅና ልማታዊነትን ለማንገስ ቀላል የማይባል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

 

እንደ መሬት፣ የመንግሥት ግዥ፣ ግብርናና ንግድ የመሳሰሉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ምንጭ ተደርገው የሚወሰዱ ዘርፎች ተለይተው በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ጥረት እየተደረገ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ልማታዊነትን ለማጠናከር መልካም አስተዳደርን ማስፈን ወሣኝ ነው።

 

መልካም አስተዳደርን ማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነትን አንድ መንገድ መዝጋትና የአገሪቱን ልማት ማፋጠን መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሥራ የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም። ጊዜን የሚጠይቅና በሂደቶች የሚከወን እንደሆነ ይታወቃል።

 

በአገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዕድገት የሚወሰነውንና በየጊዜው መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር ክንዋኔን በአንድ ጀምበር እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች በአገሪቱ መልካም አስተዳደር የለም እያሉ በተደጋጋሚ ከማስተጋባትም ባሻገር በየጊዜው የተለያዩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በማምጣትና በአገሪቱ የተረጋገጠውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማያግዝና ለማጠናከር በማይጠቅም መልክ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

 

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ፅንፈኞቹ ስለዘመሩ ሳይሆን መንግሥት በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ልማታዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው ሚናና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ቀዳሚ አጀንዳውን አድርጎ የያዘው ጉዳይ በመሆኑ ነው። መልካም አስተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ካልተቻለ ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቆ ልማታዊነትን ማረጋገጥ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ስላለው ነው።

 

መልካም አሰተዳደር በማስፈን ከፊታችን የተጋረጠውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለበርካታ አገራት የልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት የደረጀ ማህበራዊ ሥፍራ እንዳይዝና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ አፍራሽ ሚና የሚጫወት ክስተት መሆኑን የተገነዘቡ የለውጥ ኃይሎች ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ትግል የገጠሙበትም ጊዜ ሩቅ መሆኑን የሚያመለክቱ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ብዙ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያየ የዓለማችን ማዕዘን የድህነት ሥር እንዳይነቀልና ማህበራዊ ዕድገት የሚፈለገውን ያህል እንዳይፋጠን እንቅፋት ሆኖ መገኘቱ ግልጽ ነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህግጋትን እየደነገገና የመዋጊያ ሥልቶችን እየቀየሰ በጋራና በተናጥል የመንቀሳቀስ ብርታት የጨመረበት ጊዜ ነው ለማለት ይችላል፡፡

በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ የሰመረ ጉዞ ውስጥ በምትገኘው አገራችንም ኪራይ ሰብሳቢነት ሥጋት አይደለም ብሎ መከራከርና ማድበሰበስ የሚቻል አይሆንም፡፡ አገራችን ያላትን ውስን ጥሪት፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ማሣ የህዝቦቿን የመሥራት አቅም ተጠቅማ ከዘመናት ድህነት ለመወጣት የጀመረችውን ፈጣን የልማት ሩጫ በሥውር ገመድ ጠልፎ በግልጽ የሚጥል የዕድገት ጋሬጣ ስለሆነ አምርራ እየታገለችው ትገኛለች፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት በዘላቂ ዴሞክራሲና በልማት አስተሳሰብ ንቅናቄ ውስጥ ገብተው በህዳሴ ጉዞ ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ጥረት ለማምከን የሚፈታተን እፍኝ የማይሞሉ ጮሌዎች ተሰርቶ ባልተገኘ ሀብት እንዲሞላቀቁና ብዙሃን በድህነት ታጅለው እንዲቆዩ የሚደረግ አስተሳሰብና ድርጊት ስለሆነ የማስወገዱ ጉዳይ ይዋል ይደር የሚባል አይሆንም፡፡

ዛሬ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥታችን በላቀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መላው ህዝባችንን ለልማት እያነቃነቀ ሙሉ ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየሰራ የሚገኝበት አፍላ የለውጥ ጊዜ ላይ ነው።

በዚህ ረገድ አገራዊ የህዳሴ ጉዟችን ለሰመረ ህዝባዊ ስኬት እየበቃ የሚዘልቀው፣ የልማትና የለውጥ ግለት ፍጥነቱን እየጨመረ ድህነትን የተሻገረ አገርና ትውልድ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚቻለው ሲቪል ሰርቪሱ በሚወጣው ኃላፊነት ልክ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ሲቪል ሰርቪሱ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት በመፀየፍና በመዋጋት መልካም አስተዳደርን በማስፈን የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በአገርና በህዝብ ላይ ፈጣን ለውጥ እያመጣና ድህነትን ወደ ኋላ እየተወ መራመድ ያስችላል የሚል የፀና እምነት በመጨበጥና በዕለት ከዕለት ተግባር በመግለጽ የልማት ሠራዊት ቁመና ፈጥኖ በመያዝ የለውጥን መንገድ የሚመራ ኮምፓስ ሆኖ መገኘት ግድ ይለዋል፡፡

ይህ ደግሞ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የልማት ጊዜው ያቀረበው የለውጥ ጥሪ ነው፡፡ ወደ ድህነትና ኋላ ቀርነት አረንቋ ዞሮ መመለስ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ የልማት ርምጃን ማፋጠን ይጠበቃል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ደግሞ የልማት ርምጃን የሚያደናቅፍ እንቅፋት ስለሆነ እየተፈናቀለ በየመንገዱ ዳርቻ ሊጣል ይገባል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አረም እየተነቀለ በምትኩ መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገርን ለማልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ማብቃት ነው፡፡

መልካም አስተዳደር ሰፍኖ ኪራይ ሰብሳቢነት እስካልተወገደ ድረስ የቱንም ያህል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት አጢነው የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አልመው የተዘጋጁ ወርቃማ ህግጋት የልማት ፖሊሲዎችና የዕድገት ስትራቴጂዎች ቢወጡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ እናም ኪራይ ሰብሳቢነትን የማስወገድና መልካም አስተዳደርን መገንባት ይዋል ይደር ሊባል የሚችል ተግባር አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ተቋም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው የሚባሉትን አመለካከትንም ሆነ ተግባር ደረጃ በደረጃ በመለየት ለመፍታት ከምንጊዜውም የተሻለ የሥራ ግምገማ በማካሄድና ራሳችንን ወደ ውስጥ በማየት ብሎም የለውጥ አመለካከት በማስረጽ መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመድፈን የተጀመረውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት የአገራችንን ህዳሴ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ከወዲሁ በእልህና በቁጭት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተሰነዘረ ያለውን ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ታርሞ በቀጣይ በአገራችን ሠላም ሰፍኖና መልካም አስተዳደር ተረጋግጦ ማየት ነው፡፡   

መንግሥትም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ነው። ይህንን ዳር ለማድረስ ደግሞ ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። ከብረተሰቡ ተሳትፎ ውጭ መልካም አስተዳደር ሊሰፍንና ኪራይ ሰብሳቢነት ሊወገድ ስለማይችል መላው የብረተሰብ ክፍል እጅና ጓንት ሆኖ መራት ይጠበቅበታል።